አስተዳደሩ በመዲናዋ የሚስተዋሉ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመቀነስ የጊዜ ገደብ አስቀመጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝብን ለእንግልት የሚዳርግ የአገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ ነዋሪው ያነሳቸውን አንገብጋቢ ችግሮች ለመቀነስ የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ማስቀመጡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ መለሰ አለሙ ከፋና የምሽቱ ዜና መፅሄት ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ÷ የመዲናዋ ነዋሪዎች በተካሄዱ ውይይቶች ያነሷቸውን ጥያቄዎች በእቅድ በመያዝ ምላሽ የሚያገኝበት ጊዜ ተቀምጧል ብለዋል።
በዚህም ሕዝቡ ቀዳሚ እና አንገብጋቢ ናቸው ያላቸው ችግሮች እና በቀናነት ብቻ ሊመለሱ የሚችሉ ችግሮች ከውይይቱ ማግስት ጀምሮ የመፍታት ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡
ጊዜና ገንዝብ የሚጠይቁ አንገብጋቢ ጥያቄዎችም በ90 ቀናት እቅድ ውስጥ ተካተው ለሕዝብ ምላሽ የመስጠት ገደብ መቀመጡን ጠቁመው÷ ቀዳሚው የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ችግሮችን ማስወገድ ነው፤ ለዚህም ሕዝቡን የሚያማርሩ እንግልቶችን የማስቆም ስራው በ90 ቀናት መታየት እንዳለበት ግብ ተይዟል ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያለው የፀጥታ ኃይል እና አመራር ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የሚስተዋሉ ወንጀሎችን በጋራ መፍትሄ የመስጠት ስራ ሌላኛው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ነው የገለጹት አቶ መለሰ፡፡
ግንባታቸው የተቃረቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለይቶ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተገኘ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በማጠናቀቅ ለነዋሪው ማስተላለፍም በተቀመጠው ጊዜ የሚከናወን ሌላኛው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በትራንስፖርት አቅርቦት ችግር ነዋሪዎች በዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴ እየገጠማቸው ያለውን እንግልት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እና አቆራርጦ መጫን ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቀነስም ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ተግባራቱ ስለመፈጸማቸው ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አስተዳድሩ ክትትል እንደሚያደርግ ገልፀው÷ ሕዝቡም በጉዳዮቹ ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በበላይ ተስፋዬ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!