ሳዑዲ ዓረቢያ ወደ መካ የሚደረጉ ጉዞዎችን አገደች
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ ወደ መካ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ መጣሏን አስታወቀች።
የጉዞ እገዳው ሐይማኖታዊ እና መደበኛ ተጓዦችን የሚያካትት ሲሆን፥ የስርጭት አድማሱን እያሰፋ ካለው የኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ መሆኑንም አስታውቃለች።
ይህን ተከትሎም ወደ ሳዑዲ ለሐይማኖታዊ የፀሎት ስነ ስርአትም ይሁን ለጉብኝት የሚደረጉ ጉዞዎች መታገዳቸውን ገልጻለች።
ከዚህ ባለፈም የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ከተገኙባቸው ሃገራት የሚነሱ መንገደኞች ወደ ሳዑዲ እንዳይገቡም እገዳ ተጥሏል።
አመታዊው የሃጅ እና ዑምራ ጉዞ ከአምስት ወራት በኋላ ይካሄዳል፤ በአመታዊው ሃይማኖታዊ ስነ ስርአት ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ መካ ያቀናሉ።
የአሁኑ የጉዞ እገዳ እስከ ሃጅ ዑምራ ጉዞ ስለመቆየት አለመቆየቱ ግን የተባለ ነገር የለም።
ከቻይናዋ ውሃን ከተማ የተነሳው ኮሮና ቫይረስ የስርጭት አድማሱ እያሰፋ ስለመምጣቱ ይነገራል።
ቫይረሱ በመንገደኞች አፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካ የገባ ሲሆን፥ በአውሮፓም ከጣሊያን በመነሳት እየተስፋፋ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ሃገራት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ምንጭ፡-አልጀዚራ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision