ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ተወካዮች ጋር ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መከረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በፈረንሳይ ሊዮን በኢንተርፖል ዋና ጽህፈት ቤት ተገኝተው በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም የአውሮፓ ፖሊስ ህብረት፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች፣ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች እና በኢንተርፖል በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የህብረቱ ሀገራት ያቀረቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና በሰው አካል የመነገድ ወንጀልን ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የህብረቱ ሀገራት ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ እና መረጃ እየተለዋወጡ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ከኢንተርፖል ዋና ፀሀፊ ዩርገን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በኢንተርፖልና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መካከል የነበረው የስራ ግንኙነት በኮቪድ ምክንያት መቀዛቀዙን ለማስተካከል በሚያስችል ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢንተርፖል ዋና ፀሀፊ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ሀሳብ አንስተው ከተወያዩ በኋላ÷ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!