Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውጤታማ የመረጃ ስምሪት ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክ እይታውን ካጋጠመው ሀገራዊ የደኅንነት ስጋት አንፃር በመቃኘት ውጤታማ የመረጃ ስምሪት ማድረጉን ገለጸ።
አገልግሎቱ የ2014 የሥራ ዘመን የግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ላይ ጥልቅ ግምገማ በማድረግ በቀጣይ ተግባራት ላይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በመግለጫው እንዳለው፤ ባለፉት 6 ወራት በአሸባሪው ህወሓት የተሰነዘረው ጥቃት ከፍተኛ ሀገራዊ የደኅንነት ስጋት የደቀነባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር፡፡
ከውጭ ኃይሎች በተከፈተ የተቀናጀ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሃይል ሚዛንን ለማሳጣት ሙከራ መደረጉን አስታውሶ፤ በህዝብ ምርጫ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ዝግጅት በተጠናቀቀበት ወቅት ሀገራዊ የደኅንነት ስጋቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረትና መንግሥታዊ ስልጣን በድርድር እንዲያዝ የሚደረግ ግፊት ከመጨመሩ ባሻገር የተለያዩ ታጣቂዎች የስጋት ምንጭ እንዲሆኑ እድል መፍጠሩን አመልክቷል፡፡
ተግዳሮቶቹ አጠቃላይ ፖለቲካዊ ውጥረትና የጸጥታ ችግር ቢደቅኑም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አውዳዊ ሁኔታዎችን በመገምገም ስትራቴጂክ እይታውን ካጋጠመው ሀገራዊ የደኅንነት ስጋት አንፃር በመቃኘት ውጤታማ የመረጃ ስምሪት ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህም የሀገርን ህልውናና ሉዓላዊነትን ያስጠበቀ ድል መመዝገቡን አብራርቷል፡፡
አገልግሎቱ በውስጥና በውጭ ሃይሎች በተቀናጀ መንገድ የተከፈተውን ጥቃት በመመከት ረገድ ለፌዴራልና ለክልል የጸጥታ ተቋማት የመረጃ ማዕከል በመሆን የማስተባበር ሚናውን መወጣቱን ጠቁሟል።
እንደ ሀገር ተደቅኖ የነበረውን የህልውና ስጋት መቀልበስ ያስቻለ ውጤታማ የመረጃ ስምሪት መከናወኑንም አመልክቷል፡፡
በተለይም የመረጃ ኦፊሰሮችና አመራሮች የስጋት ቀጣናዎች ድረስ ዘልቀው በመግባት መረጃ በመሰብሰብና አመራር በመስጠት ያበረከቱት አስተዋጽዖ ለድሉ የማይተካ ሚና ማበርከቱን ጠቁሟል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከወራሪው የህወሓት ኃይል ጋር የተያያዙ የተለያዩ ወታደራዊ ምስጢሮችን፣ ድብቅ ሴራዎችንና የሽብር እቅዶችን የሚያጋልጡ መረጃዎችንና ሰነዶችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና ተንትኖ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ እንደ ሀገር ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ተቋማዊ ተልዕኮውን መወጣቱን የገለጸው መግለጫው፤ ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉም መደረጉንም ጠቁሟል፡፡
የሸኔንና የሌሎችንም ታጣቂዎች እንቅስቃሴዎች ለመግታትም ተቋሙ የመረጃ ስምሪት በመስጠት ሊደርሱ የሚችሉትን ከፍተኛ አደጋዎች ማስቀረቱን የጠቆመው መግለጫው፤ በዚህ ረገድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል፡፡
የሽብር ቡድኑን የግንኙነት መረብ በምስጢራዊ ክትትል በመለየት በርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ እና ማስረጃ በመሰብሰብ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራም ማከናወኑን አመልክቷል፡፡
ከውጭ የሚቃጣ የሽብርተኝነት አደጋን በመከላከል ረገድ አልሸባብና አይኤስ የሚያደርጉትን ምልመላ፣ ስርገት፣ስልጠናና እንቅስቃሴ በተመለከተ መረጃዎችን በመሰብሰብ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ አመልክቷል፡፡
በዚህም 14 የአልሸባብ እና 36 የአይኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
ህገወጥ የጦር መሣሪያዎችን እና የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን በመከላከል ረገድም ውጤታማ ኦፕሬሽኖች መካሄዳቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በተከናወነ ክትትልና ኦፕሬሽን ግምታዊ ዋጋቸው እና ወቅታዊ የምንዛሪ ተመናቸው 560 ሚልዮን ብር የሚያወጡ፤የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣የኮንትሮባንድ እቃዎች፣ ወርቅ፣ አልማዝ፣ እና ሌሎች በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡና ሊወጡ ሲሉ የነበሩ ቁሶች እንዲሁም 173 ሺ 132 የተለያዩ ጥይቶች፣95 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ 75 ብሬን መትረየሶች፣ 246 ሽጉጦች፣ 26 መገናኛ ሬዲዮኖች እና በህገወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ 177 ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉንም እንደአብነት አንስቷል፡፡
በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት በአንድ በኩል ፕሮፌሽናል፣ትውልድ ተሻጋሪ፣ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ ብቁ የሰው ኃይል ያለው ተቋም ከማደራጀት ባሻገር ተልዕኮን የሚደግፉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ያመለከተው መግለጫው፤በቀጣይም የማስፈጸም አቅምን የሚያዳብሩ ስትራቴጂክ ጉዳዮችን በመለየት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ ጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሀገራዊ አቅምን በማስተባበር እና በማቀናጀት ትላልቅ ሁኑቶች ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ የመሪነት ሚና መጫወቱን ያመለከተው መግለጫው፤ ሀገራዊ ምርጫው፣ የመንግሥት ምስረታ ሥነስርዓቱ፣ የተለያዩ የአደባባይ በዓላትና በቅርብ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በስኬት በተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ የተደረጉት የደኅንነት ስምሪቶች የተቋሙን ስኬታማ አፈጻጸም የሚያሳዩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተቋማዊ ተልዕኮን በብቃት የሚወጡ ባለሙያዎችን በመረጃና ደህንነት ኪነሙያ በማሰልጠን ለስምሪቱ ውጤታማነት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን መግለጫው አብራርቷል፡፡
ለፀጥታ አካላትና ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ስልጠና በመስጠት በተቋሙ የዳበረውን እምቅ አቅም ማጋራት ከመቻሉም ባሻገር፤ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር የመረጃ ኦፊሰሮችንና አመራሮችን በማሰልጠንም ማስመረቁን አመልክቷል፡፡
ይህም ወደፊት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በአፍሪካ የመረጃ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ጥንስስ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በቀጣዮቹ ጊዜያት ተለዋዋጭና ውስብስብ ከሆነው ሀገራዊ የደኅንነት ስጋት አንጻር አደጋን አስቀድሞ በማወቅ ማስቀረት የሚችል ሁለንተናዊ ብቃት መገንባቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው አመልክቷል፡፡
በተለይ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በመስራት መሠረታዊ ፍጆታዎችን ባልተገባ ዋጋ ለመሸጥ ከሚሞክሩ አካላት ጋር በተያያዘ የችግሮቹን ምንጮች በመለየት የህግ ተጠያቂነት ማስፈን፤ ፖለቲካዊ ችግሮች ወደ ሀገራዊ የደኅንነት ስጋት እንዳይሸጋገሩ በመረጃ ስምሪት ማገዝ፤ከውጭ ሊቃጡ የሚችሉ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን በመለየት አስቀድሞ ማክሸፍ የሚያስችል የውጭ መረጃ ስምሪትን ማጠናከር እና ወቅታዊ የደኅንነት ስጋት እየሆነ የመጣውን የመረጃ ጦርነት የሚመክት አቅም መፍጠር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.