መንግስት ያስተላለፈው የሰላም ውሳኔ ተቀባይነት ያለው እርምጃ መሆኑን የተለያዩ አገራት ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ አገራት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለማሳለጥ ይቻል ዘንድ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አድንቀዋል።
አውስትራሊያ፥የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ይቻል ዘንድ ግጭት ለማቆም ያሳለፈውን ውሳኔ እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡
በአካባቢው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ሁለቱ ወገኖች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል ስትል ጥሪ አቅርባለች፡፡
በተመሳሰይ ስዊድን፥የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ያሳለፈው የሰላም ውሳኔ ተቀባይነት ያለው እርምጃ መሆኑን ገልጻለች፡፡
ውሳኔው የታለመለትን ግቡ ይመታ ዘንድም ሁሉም ወገኖች ሃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ነው ያሳሰበችው፡፡
ስዊድን በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የምታደርገውን የሰብዓዊ እርዳታ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማስታወቋንም በኢትዮጵያ ከሚገኘው የስዊድን ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡