ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት በትኩረት ይሰራል- የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት በጥብቅ የሚሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግሥት ሃብት አስተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሲሪንቃ ግብርና ምርምር ሐይቅ ንዑስ ማዕከል የተጠለሉ ወገኖችን ጎብኝተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ከሰፈሩ 34 ሺህ ተፈናቃዮች መካከል 29 ሺህ የሚሆኑት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በመጠለያ ጣቢያው የተሟላ ቀለብ እንደማይቀርብላቸው፥ የሚቀርበውም በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን የገለጹት ተፈናቃዮቹ÷ መንግስት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በኦነግ ሸኔ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የዞንና ወረዳ አመራሮች የታገዘ መፈናቀል የደረሰባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
“በመሥራት ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የምንተርፍ ነበርን” ያሉት ተፈናቃዮቹ÷ ተቸግረን የሌሎችን እጅ ጠባቂ በመሆናችን የሞራልም ጉዳት ደርሶብናል” ብለዋል።
አሁንም በወለጋ አካባቢ በርካታ ወገኖች መንገድ ተዘግቶባቸው በከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው መንግስት ሊደርስላቸው ይገባል ነው ያሉት ተፈናቃዮቹ።
በዜጎች ሞትና መፈናቀል ዙሪያ ከፀረ-ሰላም ኃይሎች በተጨማሪ በየደረጃው ያሉ አንዳንድ የአመራር አካላት እጅ ሊኖርበት ይችላል ያሉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል÷ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ጥቃቶች በሁሉም አቅጣጫዎች በአንድ ጊዜ ተከፍተው አስቸጋሪ ቢመስሉም በዚህ አይቀጥሉም፤ ችግሮችን በጊዜ ሂደት እንፈታቸዋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ጽንፈኞች የሚያደርሱት ሰቆቃና በደል የወጡበትን ማህበረሰብ ጭምር የሚያጠቃ መሆኑንም ገልጸዋል።
ችግሩ በዚህ እንደማይቀጥል ገልጸው፥ መንግስትም የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግሥት ሀብት አስተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ÷ የጥፋት ኃይሎች እኩይ ተግባር መጠኑ የሚለያይ ቢሆንም የትኛውንም ማህበረሰብ የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አለመሆኑን ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ወገኖች እንዳይፈናቀሉ፣ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱና ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ሰርተው እንዲኖሩ ማድረግ የመንግስት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል ንፁሃንን እየገደሉ፣ እያፈናቀሉና ሀብታቸውን እያወደሙ ያሉ የግጭት ነጋዴዎች በዚህ አይቀጥሉም ያሉት ዶክተር ግርማ÷ የክልሉ መንግስት የዚህን ወንጀል ተዋናዮች ለማጥፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።