Fana: At a Speed of Life!

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተጠለሉ ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋሙ ስራ ትኩረት እንዲሰጠው የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ የሁለተኛ ቀን ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ባነሱት ጥያቄ÷ “ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን በምን መልኩ ነው ለማቋቋም እየተሠራ ያለው፣ ትኩረት አልተሰጣቸውም፣ የተደራጀ መረጃም የለም፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምን ታስቧል፣ የቡሬ ወለጋ መንገድ መቼ ይከፈታል?” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በተመሳሳይ “የኅብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና ግብዓቶችን ለነጋዴ ነው እያከፋፈሉ ያሉት፣ ይህን ሕገ ወጥ አሠራር ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አኳያ ምን እየተሠራ ነው፣ የጤና መድህንን በሚመለከት በጤና ጣቢያዎች መድሃኒት የለም፤ የተመዘገቡት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አለ፣ ምን እየተሠራ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡
የአሸባሪውን ቡድን ወረራ ለምን በፍጥነት ማጠናቀቅ አልተቻለም፣ የአሸባሪው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ከእስር ለምን ተፈቱ፣ የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካን ለመገንባት 300 አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ተፈናቅለው ካሳ ባለመከፈሉ እስካሁን ሥራ አለመጀመሩን አንስተዋል፡፡
አርሶ አደሮችም ለተነጠቁት መሬት ለምን ግብር ይከፍላሉ፣ ፋብሪካው ያለበትን ቸግር ፈትቶ ወደ ስራ እንዲገባ ምን እየተሠራ ነው የሚሉ ጥያቄዎችም በምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል፡፡
አብን በክልሉ መንግስት በቂ ተሳትፎ እያገኘ አይደለም፣ ከመንግስት ጋር የሚሰራበት አሰራርም አልተዘረጋም ያሉት የምክር ቤት አባላቱ÷ የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ ፣ ለልማት እና ለተፈናቃዮች የወጣው ንብረት ኦዲት ተደርጎ ለህዝብ እንዲቀርብም ጠይቀዋል፡፡
ከትግራይ የተፈናቀሉ ወገኖች በተለይ በምስራቅ አማራ አካባቢ እየገቡ ነው ይህም የዳግም ወረራ ስጋት የለውም ወይ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ በክልሉ ያለው ሁኔታ በሪፖርቱ ለምን አልተካተተም፣ በአሸባሪው ቡድን ወረራ ምክንያት ያልለማው መሬት በግብርናው ዘርፍ አልተካተተም፣ የጦርነቱን ተጽዕኖ በሪፖርቱ አልተመለከትንም የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ የሥራ እና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ በክልሉ ከ109 ሺህ በላይ ምሩቃን ስራ አጥ መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ችግሩን ፈጥኖ ለመፍታት ያልተቻለው የቅድመ ሥራ ተግባራት አለመከናወናቸው እና የክልሉም ዋና ትኩረት የኅልውና ዘመቻው እንደነበር በምክንያትነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ ለወጣቶች የተሰጡ ብድሮች በወቅቱ ባለመመለሳቸው ሌላ ብድር ለመስጠት ፈተና ቢሆንም÷ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም 400 ሚሊየን ብር ብድር መስጠት መቻሉን አመላክተዋል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩል በብድር የተወሰደ ገንዘብ በተገቢው መልኩ ሳይመለስ ሌላ ብድር ለመስጠት የፋይናንስ አሠራሩ ስለማይፈቅድ በዚህ ላይ የተቀናጀ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሥራ ፈጣሪ ተቋማት ለምሳሌ የማዕድን፣ የቱሪዝም፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርና እና ሌሎችም ዘርፎች በዕቅድ በተካተተ መናበብ ሊሠሩ እንደሚገባ የቢሮው ኃላፊ አሳስበዋል። የሥራ ባህልን በማዳበር ከጠባቂነት በመውጣት ሥራ ፈጣሪ መሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
አቶ አረጋ አክለውም፥ ቢሯቸው የማስተባበር ኃላፊነት እንዳለው ጠቁመው÷ ሥራ የሚፈጥሩት ሌሎች ተቋማት መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በተቋማት መካከል መናበብ አለመኖሩም ያጋጠመ ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከትምህርት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ÷ ቢሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ሂደት በተመለከተ ተማሪዎች ፈተና ሲወስዱ ጀምሮ ጥያቄና ቅሬታ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው÷ ጉዳዩን የሚከታተል አጣሪ ኮሚቴ በማቋቋም ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ተማሪዎች ከጦርነት ስነ ልቡና በደንብ ሳያገግሙ መፈተናቸው ተጽእኖ መፍጠሩን ገልጸው÷ ትምህርት ሚኒስቴር ግን ጦርነቱ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤት ላይ ተጽዕኖ የለውም ማለቱ ሣይንሳዊ አይደለም ብለዋል። ጉዳዩ በከፍተኛ ትኩረት ታይቶ መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡
ግብርናን በተመለከተ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃ/ማርያም ከፍያለው በሰጡት ምላሽ÷ የማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ ለዘንድሮ የመኸር ምርት ከሚያስፈልገው 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን ክልሉ ያገኘው አንድ ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው ብለዋል።
ችግሩን ለመቅረፍም እንደ ኮምፖስት ያሉ የተፈጥሮ ማዳበሪዎችን የመጠቀም ግዴታ ውስጥ መገባቱን ጠቁመው÷ የመስኖ አካባቢዎች ላይ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያን ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተገኘውን ማዳበሪያም በኮታ ሳይሆን÷ የምርት ወቅትን እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ታሳቢ በማድረግ በፍትሃዊነት ይሰራጫል ብለዋል፡፡
የመሰረተ ልማትን በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በሰጡት ማብራሪያ ÷ አዳዲስ የተጀመሩ የአስፋልት መንገዶች በሰላም እጦት መዘግየታቸውን ገልጸው÷ ከፌደራል መንገዶች አስተዳደር ጋር በመነጋገር እንዲጀመሩ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡
መብራትን በተመለከተም በዋግኽምራ እና በሌሎችም አካባቢዎች ስፋ ያለ ችግር መኖሩን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ለክልሉ 22 ንጸ ጣቢያዎች እንዲገነቡ የተፈቀደ መሆኑን ገልጸው ከነዚህ መካከል ስድስቱ በግንባታ ስራ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በተለይም በመስኖ ልማት ከተያዘ በጀት በተጨማሪ 170 ሚሊየን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ እንደገለጹት÷ በመስኖ ስንዴ 41 ሺህ ሄክታር እየለማ ሲሆን የመስኖ ልማት ሥራውንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው ያመላከቱት፡፡
በውጤታማነት የማይሠሩ የመስኖ ግድቦች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በለይኩን አለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.