Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ አፍሪካ ዳታ ሲስተም በመገንባት የሚታወቀው “የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ኢኮ ሲስተምስ” ማዕከል አገልግሎት መሥጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ፓርኮች መካከል ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው “ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ኢኮ ሲስተምስ” የተሰኘ ኩባንያ የገነባው የመረጃ ቋት ማዕከል አገልግሎት መሥጠት ጀምሯል፡፡

“ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ኢኮ ሲስተምስ” በምስራቅ አፍሪካ የመረጃ ቋት መሰረተ ልማትን በመገንባት የሚታወቅ ኩባንያ ሲሆን፥ በኢትዮጵያም አዲስ አበባ ላይ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ የገነባው ማዕከሉ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኢንተርኔት አገልግሎትን በተመሳሳይ ሠዓት መሥጠት የሚችል ነው፡፡

የመረጃ መጥፋት ችግር እንዳይኖር እንዲሁም የሲስተም መቆራረጦች እንዳይከሰቱ አስፈላጊው ቴክኖሎጂዎች በሙሉ የተሟሉለት ነው ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የማስጀመሪያ መርሃ – ግብር ላይ የ”ዊንጉ አፍሪካ ዳታ ኢኮ ሲስተምስ” ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንቶኒ ቮስካርዲስ ÷ በኢትዮጵያ መንግስት እና በተባባሪ ተቋማት ዊንጉ አፍሪካ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተቀናጀ አገልግሎት አቅራቢ የመረጃ ማዕከል ሊገነባ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ አስፈላጊው ሁሉ አገልግሎት ከጥራት ጋር በመቅረቡ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ትልቅ እምነት እና ፍላጎት እንዳደረባቸውም አክለዋል፡፡

ኩባንያው ከአቢሲኒያ እና ጎህ ባንኮች ጋር እንዲሁም ከዌብ ስፒሪክስ ሶሊዩሽንስ፣ ሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂ እና አፍሪኮም ከተሰኙ አምሥት ተቋማት ጋር አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት እንደተፈራረመ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም ኩባንያው የፕሮጀክቱን የቀጣይ ምዕራፍ ሥራዎች አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም ከሌሎች የመንግስትና የግል ተቋማት ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸውን የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.