Fana: At a Speed of Life!

ኤች አር 6600 የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከግምት ያላስገባ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምስራቅ አፍሪካ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም በሁለትዮሽና የጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።

በወቅቱም መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድርጅቶች ድጋፍ ለተጎጂዎች ያደርሱ ዘንድ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ሰብአዊ አቅርቦቱ ላይ በአሸባሪው ህወሓት መስተጓጎል መፈጠሩን እና ቡድኑ በአጎራባች ክልሎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ትንኮሳ በተመለከተም አብራርተዋል።

አቶ ደመቀ አያይዘውም ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ እና ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ያላስገባ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሜሪካም በኢትዮጵያ ሰላም እና ዴሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳውን ረቂቅ ታጸድቀዋለች የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል።

በውይታቸውም መንግስት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰዳቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተ አቶ ደመቀ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በተጨማሪም ስለተለቀቁ የፖለቲካ እስረኞች፣ በሀገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት እና በሀገሪቱ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ ገላጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በመንግስት የተወሰዱ አዎንታዊ ማሻሻያዎችን አሜሪካ ታደንቃለች ብለዋል፡፡

ልዩ ልዑኩ በቆይታቸው ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከሰብዓዊ ድርጅት ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.