Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እንሰራለን – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ በተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ዙሪያ በሐረሪ ክልል ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ መንግስት በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አይጠናቀቁም፣ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችንም ለታለመላቸው ዓላማ ከማዋል አንፃር ክፍተቶች እንደሚታዩባቸው ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች የገለጹት።
በክልሉ በሚስተዋለው ህገወጥ የመሬት ወረራ በተለይም በወረዳ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ችግሩን ከመከላከል ይልቅ ራሳቸው እየተሳተፉ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
መንግስት የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲማረር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባዋልም ነው ያሉት።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ በሰጡት ምላሽ፥ የክልሉ መንግስት ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ ያሉ አመራሮችን የማጥራት እና በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ የሌብነት ችግሮችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አንስተዋል።
የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ በተለይ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመሸጫና የማምረቻ ቦታ ለማመቻቸት ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸው÷ ከአሰራርና ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በመፈተሽ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት ይሰጣልም ነው ያሉት።
የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ያስቀመጣቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለመፈጸም ከአመራሩ በተጨማሪ ህዝቡም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ፓርቲው በህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ማሳለፉን ጠቅሰዋል።
የተነሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ፓርቲው የእቅዱ አካል አድርጎ ለመፍትሄው ይሰራል ያሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞገስ ባልቻ ናቸው።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ሀሊም ሀሰን በበኩላቸው÷ መንግስት በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በትኩረት እየሰራ ነው ማለታቸውን የሐረሪ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.