በምእራብ ሸዋ ዞን በመስኖ ከለማ መሬት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአትክልት ምርት ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምእራብ ሸዋ ዞን በመስኖ ከለማ መሬት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአትክልት ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ዲንሳ እንደገለጹት ÷ምርቱ የተገኘው ዘንድሮ በመጀመሪያ ዙር ከለማው ከ27 ሺህ 841 ሄክታር መሬት ላይ ነው።
ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ካሮት፣ ጎመን፣ ድንችና ቲማቲምና ቃሪያ በመስኖው በዋናነት መልማታቸውን ተናግረዋል።
ከ100 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በዘመናዊና ባህላዊ መንገድ ወንዞችን በመጥለፍ፣ ግድቦችንና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም በልማቱ መሳተፋቸውን አስረድተዋል።
ለልማቱ ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሁም በአርሶ አደሩ የተዘጋጀ ከ100 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አርሶ አደሩ ዝናብን ሳይጠብቅ በመስኖ በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ እያመረተ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ እንዲያቀርብ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል።
በሁለተኛው ዙር መስኖ ለማልማት ከታቀደው 24 ሺህ 380 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 18 ሺህ 962 ሄክታሩ ታርሶ በዘር መሸፈኑን ያስታወቁ ሲሆን ÷ከልማቱ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!