ኢትዮጵያ ያሏትን ተጨባጭ እውነታዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ልታጠናክር ይገባል – የሕግ ምሁራን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ያሏትን ተጨባጭ እውነታዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት የምታደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክር መቀጠል አለባት ሲሉ የሕግ ምሁራን ጠቆሙ፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ መስኡድ ገበየሁ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በገለልተኛ ተቋማት የተረጋገጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን የተካሄዱ ምርመራዎችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ ትኩረት እንዳልሰጣቸው አንስተዋል፡፡
በተለይ አሜሪካ ከበወረራ ተይዘው በነበሩ አካባቢዎችና ነዋሪዎች ላይ ከተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ውድመቶች ይልቅ ኤች አር-6600 እና ሌሎች የተናጠል ክሶች ላይ ትኩረት አድጋለች ነው ያሉት፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ አቶ መሃመድ ሰኢድ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የራሷ እውነትና ፍትሃዊ ጥያቄ ቢኖራትም የአሜሪካ ፖለቲካዊ ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጣልቃገብነትና ጫና ማሳደር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የዋሺንግተን አስተዳደርና ፖለቲከኞች አካሄድ የተዛባ ፍትሕ ማሳያ እንደሆነም ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት፡፡
ኤች አር-6600 የተሰኘው ረቂቅ ሕግ በሀገር ላይ ከሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ አንፃር እዳይጸድቅ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው ምሁራኑ በአጽንኦት ያሳሰቡት።
ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያን እውነታና ትክክለኛ ገጽታ ለተቀረው ዓለም ለማስረዳት ጠንካራ እና የተቀናጁ አሰራሮችን መተግበር እንደሚገባ ምሁራኑ ጠቁመዋል።
በጥቂት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የተዘጋጀው ኤች አር-6600፥ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚቃረን፣ የውጭ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማስቀረት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በአወል አበራ