ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ67 ሚሊየን 520 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ነው 63 ሚሊየን 877 ሺህ ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 3 ሚሊየን 642 ሺህ ብር የሚያወጡ የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የያዘው፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መሆናቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች ፣የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡