የብልጽግና ፓርቲ በመተዳደሪያ ደንቡ ባስቀመጠው አግባብ መሰረት ምርጫ በማካሄድ ጠንካራ የአመራር አደረጃጀት መፍጠር ችሏል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ በመተዳደሪያ ደንቡ ባስቀመጠው አግባብ መሰረት ምርጫ በማካሄድ ጠንካራ የአመራር አደረጃጀት መፍጠር ችሏል ሲሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ገለጹ።
የፓርቲው አመራሮች ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ ለማሻገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት፡፡
አቶ ተስፋዬ፥ የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና የፓርቲውን ውስጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ያካሄደው የምርጫ ሥርዓት “የጉባኤ ፕሬዚደም ሳይሰየም የተካሄደ ነው” በማለት በአንዳንድ አካላት የሚነሳው ትችት የፓርቲውን አሰራር እንዲሁም የጉባኤውን አጠቃላይ ሂደት ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 16 ንኡሰ አንቀጽ 3 መሰረት፤ ጉባኤውን የሚመሩት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ናቸው ይላል።
ያም ሆኖ ከዚህ ቀደም ፓርቲው ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ስላልነበሩት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጉባኤውን በማስፈቀድ መድረክ እንዲይዙ መደረጉን ጠቁመዋል።
ይህ የሆነውም ፓርቲውን የሚመሩ፣ የሚያስተባብሩ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 16 መሰረት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው የጽህፈት ቤት ሃላፊ ፕሪዚደም መያዛቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተሰየሙትም ጉባኤው ሙሉ ይሁንታ በማግኘት መሆኑንም ነው አቶ ተስፋዬ የገለጹት።
በተጨማሪ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች በጉባኤ መገኘታቸውን ጠቁመው፥ አጠቃላይ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አሳታፊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀናቁን አረጋግጠዋል።
በጉባኤው የተመረጡ የፓርቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች አሁን አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለማሻገርና ለውጡን ከግብ ለማድረስ በትጋት ይሰራሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!