የዓለም የጤና ድርጅት “የህክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል እንዳላደርስ በመንግስት ተከልክያለሁ” ማለቱ ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው-መንግስት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የጤና ድርጅት “የህክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል እንዳላደርስ በመንግስት ተከልክያለሁ” ማለቱ ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የድርጅቱን መርሆችና እሴቶች የጣሰ አካሄድ እየተከተሉ መሆኑንም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር በስዊዘርላንድ ጀኔቭ ትናንት በሰጡት መግለጫ “መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እንዳይገባ ከልክሏል” በማለት የሀሰት መረጃ ሰጥተዋል።
“በትግራይ ክልል የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ሆነዋል” በማለትም ተናግረዋል።
ሆኖም ዋና ዳይሬክተሩ የሰጡት መግለጫ ከእውነታው የራቀ እና መንግስትን በሃሰትና ባልተገባ መልኩ የወነጀለ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገልጸዋል።
የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች በአፋር ክልል ወረራ በመፈጸምና መንገድ በመዝጋት የህክምና ቁሳቁስና ሌሎች እርዳታዎች ወደ ትግራይ እንዳይደርስ እያደረጉ መሆኑ እየታወቀ ዋና ዳይሬክተሩ መንግስትን ተወቃሽ ማድረጋቸው ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት የእርዳታ መተላለፊያ ኮሪደሮችን መዝጋቱን ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አውሮፕላኖች በሳምንት ከሶስት ጊዜ በላይ ወደ ትግራይ እርዳታ እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እንዳይደርስ እያደረገ ያለው አሸባሪው ህወሃት መሆኑን በትክክል መገንዘብ አለባቸው ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ከዚህ አኳያ የዓለም የጤና ድርጅት አሸባሪውን ህወሃት በግልጽ ሊያወግዝ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ ሁሉንም አካባቢዎችን በፍትሃዊነት ከማገልገል ይልቅ ስለ አንድ አካባቢ ብቻ ትኩረት ሲያደርግ ይስተዋላል፤ ይህም ከድርጅቱ መርሆ አንፃር ትክክል አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሆነ ብለው የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እንዳይገባ እንደከለከለ አድርገው መናገራቸው ፍጹም ከእውነት የራቀ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የድርጀቱን መርሆችና እሴቶችን በጣሰ መልኩ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡