በአዲስ አበባ በመሰረተ ልማት ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፣ በኢትዮ ቴሌኮምና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኬብሎች ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፍንጅ ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኃይል ማስተላለፊያ ኬብል በመቁረጥ ሲወስዱ የነበሩ ግለሰቦች በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ንግድ ባንክ አካባቢ ተመሳሳይ ስርቆት ሲፈፅሙ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደመና ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
ከቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦ እየቆረጡ ሲወስዱ ከነበሩት ተጠርጣሪዎች መካከል ሶስቱ በወቅቱ አምልጠው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ባደረገው ጠንካራ ክትትል ከሶስት ቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማስፋት በአጠቃላይ በቀላል ባቡር የኃይል መስመር ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 9 ግለሰቦች እንዲሁም የተሰረቀውን ንብረት ለማጓጓዝ ሲጠቀሙበት የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ.አ 81673 ቪትዝ ተሽከርካሪ ተይዞ ምርመራው መቀጠሉን ተናግረዋል።
የተቆረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኬብል 100 ሜትር እንደሚረዝም እና አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ ከ161 ሺህ ብር በላይ መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ዜና ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮ ቴሌኮም የሆኑ እና ከልዩ ልዩ ቦታዎች የተሰረቁ ኬብሎችን አከማችቶ የተገኘ ግለሰብ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!