የቤተ መንግስት ይዞታዎችን ወደ ልማት ለማስገባት እየሰራ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስሩ የሚገኙ ይዞታዎችን ወደ ልማት ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የኢፌዲሪ ቤተ መንግስት አስተዳደር አስታወቀ።
የቤተ መንግስት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ዴሬሳ እንደገለጹት÷ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምንም አይነት ልማት ሳይከናወንባቸው ለዘመናት የተቀመጡ ሰፋፊ የቤተ መንግስት ይዞታዎችን ወደ ልማት ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በአዋሽ መልካሳ ቤተ- መንግስት ይዞታ በሆነው በ200 ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን ጠቅሰው÷ በተመሳሳይ በቆቃ ቤተ መንግስት ይዞታ በሆነው 100 ሄክታር መሬት ላይም ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በእነዚሁ የቤተ መንግስት ይዞታዎች ከፍራፍሬና ስንዴ ልማት ጎን ለጎን ከ10 ሚሊየን በላይ ዶሮ በማርባት የስጋ ዶሮና እንቁላል ለገበያ ለማቅረብ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ በገበያ ላይ ዋጋቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሸማቹ ማህበረሰብ ምርቱን በቀላሉ እያገኘ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ÷ በዘርፉ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጭምር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡
በቆቃ ሐይቅ ላይ በአመት ከ40ሺህ ቶን በላይ አሳ ለማምረት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመው÷ በቂ የአሳ ምርት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ስራ እየሰራን ነው ሲሉም አክለዋል።
በተለይ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱካምና አዲስ አበባ ከተሞች በመጭው አመት የአሳ ምርት ለገበያ ማቅረብ እንደሚጀመር ተናግረዋል ።
በአካባቢው ያለውን የአሳ ምርት አቅርቦት እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ በከተሞቹ የአሳ ፍላጎትን ለማሟላት ጭምር ፕሮጄክት ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ዳይሬክተሩን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል ።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!