በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰበትን የፋይበር ኦፕቲክስ መስመር እየተጠገነ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው በምስራቅ አማራ እና በአፋር የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የተጎዱ የፋይበር ኦፒቲክስ መስመሮችን የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ገብረ መድህን እንደገለጹት÷ ከኮምቦልቻ- ሰመራ፣ ከሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ፣ ከኮምቦልቻ- አላማጣ እንዲሁም ከኮምቦልቻ- አቀስታ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ምሰሶዎች አናት ላይ ተዘርግተው በሚገኙ የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች ላይ ህወሓት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮቹ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መከላከያ ከመስጠት ባለፈ÷ ለቴሌኮሙኒኬሽን ሥራዎችና ከኃይል ማመንጫ እንዲሁም ማከፋፈያ ጣቢያዎች መረጃዎችን ወደ ብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ለማድረስ ያግዛሉ፡፡
መስመሮቹ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያሉ መረጃዎችን መሰብሰብና መመልከት አለመቻሉን ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
የፋይበር ኦፕቲክስ የጥገና ስራ ጥንቃቄን የሚጠይቅና አድካሚ ቢሆንም÷ አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ በወቅቱ ለማድረስ ሁሉም ሠራተኛ በከፍተኛ ተነሳሽነት የጥገና ስራውን እያከናወነ ይገኛል መባሉን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአካባቢው ያለው ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘው ከረጅም ጊዜ በኋላ በመሆኑና ለጥገና ሥራ በሚል ኤሌክትሪክ በተከታታይ እንዳይቋረጥበት ታሳቢ በማድረግ÷ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ኤሌክትሪክ በማቋረጥ ጥገናው እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የአማራና አፋር ክልሎችን በወረራ ይዞ በቆየባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የማስተላለፊያ መስመሮች መካከል በ53 ነጥብ 3 በመቶው ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!