የኮሮና ቫይረስን ስጋት ለመቀነስ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
የአዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተቋሙ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያከናወናቸው ባሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ዙሪያ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ካሳለፍነው ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሁሉም የሃገሪቱ መግቢያ ጣቢያዎች ከ324 ሺህ በላይ መንገደኞች በሙቀት ልየታ ማለፋቸውን አንስተዋል።
በአሁኑ ስዓት 829 ለሚሆኑ መንገደኞች ክትትል እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ 12 አዳዲስ ጥቆማዎች ለኢንስቲትዩቱ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በሁሉም ጥቆማዎች ላይ በተደረገ ማጣራት ሁሉም የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ መሆናቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በቫይረሱ ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ ክትትል የሚደረግለት ሰው አለመኖሩን ዶክተር ኤባ ጠቁመዋል።
ቫይረሱ በአሁኑ ወቅት ከቻይና ባሻገር በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተስፋፋ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከምን ጊዜውም በላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከቻይናና በሽታው ሪፖርት ከተደረገባቸው ሃገራት የመጡና የበሽታው ምልክት የታየባቸው ዜጎች ሲመለከቱም በነጻ የስልክ መስመር 8335 በመደወል ጥቆማ እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በቅርቡ በቻይና ውሃን ከተማ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን 2 ሺህ 698 ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ፥ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።
ቫይረሱ አሁን ላይ የሥርጭት አድማሱን በማስፋት 34 በሚደርሱ የዓለም ሀገራት ውስጥ መከሰቱ ተነግሯል።
በሃይማኖት እያሱ