ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “ጉዞ ወደ ሀገር ቤት “ጥሪ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድህረ ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት የዳያስፖራ ተሳትፎን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ።
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ ዳያስፖራው ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ በነበረችባቸው አስጨናቂ ጊዜዎች ላደረገው ድጋፍና ላስገኛቸው ውጤቶች ምስጋና አቅርበው አሁንም ሀገራዊ ፈተናዎቹ እስኪወገዱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚሲዮኖችና ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራታቸውን እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል፡፡
የዳያስፖራውን ዕምቅ አቅም ከመጠቀም አንጻር ከተሰራው ይልቅ ወደፊት ሊሰራ የሚገባው ብዙ ነገር እንዳለ የጠቆሙት አቶ ደመቀ፥ ጥሪውም በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙና በታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት መርሀ ግብሮች ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የፌዴራል ባለድርሻ አካላትም ከዳያስፖራው ጋር በመተባበር በየዘርፋቸው እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል።
በቀጣይም በመልሶ ግንባታ፣ በዕውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፍ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚሲዮኖች በኩል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮችም አቅርበዋል።
የሚሲዮን መሪዎች በበኩላቸው፥ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲቻል ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፥ ጥረታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በማዕከል ደረጃ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ፥ ዳያስፖራውን የኢኮኖሚ አምባሳደርና የመልሶ ግንባታ አጋር ማድረግ ከሚሲዮኖች የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን አንስገንዝበዋል።
ኤጀንሲው በሚሲዮኖችና ባለድርሻ አካላት የተነሱና የዳያስፖራን ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ስትራቴጂያዊ ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች በመለየት መፍትሔ ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።