Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ያልሰከነው የፖለቲካ አውድ ለሕግ አስከባሪዎችና ለፍትህ ተቋማት ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል – ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ያልሰከነው የፖለቲካ አውድ ለሕግ አስከባሪዎች እና ለፍትህ ተቋማት ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ተናገሩ።

የፍትህ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዳማ እየተካሄደ በሚገኘው የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ አቃቤያነ ሕግ የጋራ መድረክ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች እየተፈተነች ቢሆንም የተጀመረውን ሀገራዊ የእድገት ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የፍትህ ተቋማት ሚና ጉልህ ነው ተብሏል።

እንደሀገር ወጥነቱን የጠበቀ እና ጥራት ያለው የፍትህ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግም ተገማች፣ ተቀራራቢ እና ቀልጣፋ የሕግ ውሳኔዎች ሊተላለፉ ይገባል መባሉን የዘገበው ኢቢሲ ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች በጋራ መስራት እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አዘጋጅነት በተካሄደው የጠቅላይ ዐቃቢያነ ሕግ የጋራ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የተለያዩ የፌደራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ፥ በክብር እንግድነት የተገኙት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ የፍትሕና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ተሳትፈዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ፥ ወጥና ቀጣይነት ባለው መንገድ በመገናኘት በተናበበ መልኩ ሕዝብን ማገልገል የሚያስችል ጠንካራ አሰራር ዘርግቶ በጋር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዜጎች በየትኛዉም የኢትዮጵያ ክፍል ቢገኙ የህግና ፍትሕ ስርዓቱ መብትና ጥቅማቸዉን የሚያስጠብቅ እንዲሁም ተደራሽና ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ ሊሆን እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፖለቲካ ለውጡ ጋር ተያይዞ በህግና ፍትሕ ዘርፉ የታዩ በጎ ለውጦችና ጅምሮች ቢኖርም በዚያው ልክ ክፍተቶች እንዳሉ የማይካድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፥ ጠንካራ፣ ውጤታማና ዘላቂ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራርን መዘርጋት እንዲሁም ቅንጅታዊ አስራሩ ቋሚና ተከታታይ የሆነ የግንኙነት መድረኮች ያሉት፣ በበላይ አመራሮች ቢቻ ሳይሆን በየደረጃው ባሉ የሥራ ኃላፊዎች መካከል ሊኖርና የዜጎችን የፍትህ ጥማት ማዕከል ያደረገ ሊሆን ይገባል ተብሏል፡፡

ለዚህም እንዲረዳ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን፣ የተናበበና የተቀናጀ ሀገር አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ እንዲኖር ማድረግ፣ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድርግ፣የማህበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት ማስፈን እንዲሁም የሽግግርና የተሃድሶ ፍትሕ አማራጮችን መተግበር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በመድረኩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን ፥ የአሰራር ስርዓት ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ከመሆኑም በላይ የጋር መግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ የፊሪማ ስነ-ስርዓትም ተካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.