የኩላሊት እጥበት የሚሰጥባቸው የመንግስት የህክምና ተቋማት የግብዓት እጥረት አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኩላሊት እጥበት የሚሰጥባቸው የመንግስት የህክምና ተቋማት የግብዓት እጥረት አሁንም ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ተገልጿል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባደረገው ቅኝት፤ የህክምና ግብዓት እጥረት የኩላሊት እጥበት ህክምናን ለመስጠት ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ተመልክቷል።
የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኩላሊት እጥበት የሚሰጥባቸው ማእከላት ከዘጠኝ አይበልጡም።
አሁን የኩላሊት እጥበት እየተሰጠባቸው ከሚገኙት የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ አራቱ በአዲስ አበባ፤ በክልል ከሚገኙት ደግሞ የባህርዳር ፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዱ ነው።
ሆስፒታሉ ባሉት 12 አልጋዎች በ3 ፈረቃ የእጥበት አገልግሎትን እየሰጠ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል።
ይሁን እንጂ ገና እጥበቱን ያልጀመሩና ወረፋ የሚጠብቁ ከ30 በላይ ህሙማን ያሉ ሲሆን፥ ከ10 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወረፋውን በመጠበቅ ላይ እንዳሉ ህክምናውን ሳያገኙ ህይወታቸው አልፏል።
ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው ችግር የግብአት እጥረት መሆኑን ነው የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አብይ ፍስሃ ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ስፔላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት የሚጠብቁ ታካሚዎችም በርካቶች መሆናቸውን ተመልክተናል።
የፈለገ ህይወት ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ቅዱስ ጳውሎስ ስፔላይዝድ ሆስፒታልን እንደ ማሳያ አነሳን እንጂ እንደ ሀገር የኩላሊት ህሙማን እየጨመሩ ቢሆንም የህከምና አገልግሎቱ ግን እየተስፋፋ አይደለም።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የግብአት እጥረት መሆኑን ነው በጤና ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተ ጀኔራል አቶ ያእቆብ ሰማን የሚናገሩት።።
የግብአት እጥረቱ እየተፈጠረ ያለውም በሀገር አቀፍ የግዥ ሬጉላር ላይ ግብዓቶቹ ባለመመዝገባቸው መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
እስከ 2012 መጨረሻ 10 ሆስፒታሎች ላይ አገልግሎቱ እንዲሰጥ ለማድረግ እና የግብዓት እጥረቱን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ያእቆብ አንስተወል።
ግብአቶቹ በሀገር አቀፍ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች ግዥ እንዲካተቱ የማደርግ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግም ሌላው መፍትሄ ሆኖ ስራዎች እየተከወኑ ነው ተብሏል።
የኩላሊት እጥበት (ዳያሊስስ) ማእከላትን ቁጥር በሚቀጥለው ዓመት ወደ 24 ለማድረስም እየተሰራ ነው ብሏል ጤና ሚኒስቴር።
በተጨማሪም የንቅለ ተከላ ማእከላትን ማስፋት ዘላቂ መፍትሄ በመሆኑ አሁን በቅዱስ ጳውሎስ ስፔላይዝድ ሆስፒታል ብቻ እየተሰጠ ያለውን የንቅለ ተከላ ህክምናም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት እየተሰራ ነው።
ጥቁር አንበሳ፣ መቐለ ዐይደር ሆስፒታል እና ባህርዳር ሆስፒታሎች ደግሞ የንቅለ ተከላ ማእከላትን ለመክፈትም እንቅስቃሴ እየተደረገባቸው መሆኑ ተመላክቷል።
እንዲሁም በቀጣይ በ10 ማእከላት የንቅለ ተከላ ህክምና እንዲሰጥ የማድረግ የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዟል።
በዙፋን ካሳሁን