Fana: At a Speed of Life!

ከጉባኤው አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የጀመረችውን ትግል የሚያጠናክር ውሳኔ እንጠብቃለን-ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 35ኛው የህብረቱ ጉባኤ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የጀመረችውን ትግል የሚያጠናክር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ እንጠብቃለን ሲሉ ምሁራን አመለከቱ።
 
በተለያዩ አካባቢዎች በ2ኛ ደረጀና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በታሪክ መምህርና ተመራማሪነት ከ36 ዓመታት ያገለግሉት አቶ ዱርኦ ጉባ እንደገለጹት÷ቀደምት የአፍሪካ ልጆች አህጉሪቱን ከቅኝ ገዥዎች ጫና በማላቀቅ ነጻነቷን ለማስጠበቅ የተለያዩ ትግሎችን አካሂደዋል።
 
በተለይ የኢትዮጵያው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ የጋናው ዶክተር ክዋሚ ንኩሩማህ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ እና ሌሎች የአፍሪካ ልጆች የአፍሪካን ማንነት ወደቀድሞ ለመመለስ ውጤታማ ትግል ማድረገቸውን አስታውሰዋል።
 
በዚህም የአፍሪካን ማንነት፣ ባህልና ወግ ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
 
ድርጅቱም የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታትና የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጫና በጋራ ለመከላከል አቅም መፍጠሩን አውስተዋል።
 
አፍሪካዊያን 35ኛው የህብረቱ ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰናቸው ለእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ እድል እንደማይሰጡና ትግላቸው ግልጽ መሆኑን ያሳዩበት ነው ሲሉም አስረድተዋል።
 
በኢትዮጵያ ላይ ጫናውን ለማጠንከርና ስሟን ለማጉደፍ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው አፍሪካዊ እንድነትን ለማጠናከር ያላቸውን ጽኑ እምነት ዳግም ያሳዩበት መሆኑን የገለጹት አቶ ዱርኦ÷በ35ኛው የህብረቱ ጉባኤም አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የጀመሩትን ትግል የሚያጠናክሩበት ውሳኔ ይተላለፍበታል ብለው እንደሚጠብቁ አንስተዋል፡፡
 
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ መሳይ ፍቅሩ በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ የሕብረቱ ጉባኤ ይዞት የሚመጣውን ዲፕሎማሲያዊ ድል በተሻለ መልኩ ለመጠቀም መስራት አለባት ብለዋል፡፡
 
የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ በኢትዮጵያ ሰላም የለም በሚል ሲናፈስ የነበረው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ጫና በአፍሪካዊያን ያለመንበርከክ ቆራጥ ውሳኔ መክሸፉ የትግል ምዕራፉን ታሪካዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
 
ኢትዮጵያ አጋጣሚውን በመጠቀም ሰላማዊ፣ የተረጋጋችና የቱሪዝም መዳረሻ አገር መሆኗን ለዓለም ህዝብ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ መስራት ይገባታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.