Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓለም የማዕድን አውጪ ኩባንያዎች ተፈላጊ መዳረሻ የመሆን አቅም እንዳላት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓለም አቀፉ የማዕድን አውጪ ኢንዱስትሪ ውስጥ በዘርፉ በተሰማሩ የውጪ ኩባንያዎች ተፈላጊ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን አቅም እንዳላት ተገለጸ፡፡

ማይን የተሰኘ በዘርፉ መረጃዎችን የሚያወጣ ድረ-ገጽ፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን ክምችት ያላትና በመልካም የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኝ የመንግስት አስተዳደር የተመሰረተባት ሀገር ናት ብሏል፡፡

ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ (EITI) የተሰኘ በማዕድን ዘርፍ ላይ የሀገራትን የማዕድን ምርት ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ የሚያደርግ ድርጅት በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አዋጪ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

ተቋሙ በሪፖርቱ፥ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 19፣ 3 ነጥብ 23 ቶን ወርቅ በዓለም ገበያ ሸጣ 126 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር አግኝታለችም ነው ያለው፡፡

እስካሁን ባለው የማዕድናት ወጪ ንግድም ወርቅ 93 በመቶውን በመሸፈን ጎልቶ እንደወጣ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የማዕድን አውጪ ኢንዱስትሪዎች የሚስብ በርካታ ዓይነት የማዕድናት ክምችት እንዳላት ጠቁሞ በቀጣይ በዘርፉ የሚስተዋለውን ያልተመጣጠነ እና በወርቅ ላይ ያተኮረ የወጪ ንግድ ለማስተካከል በዘርፉ ለተሰማሩ የውጪ ኩባንያዎች በሯን መክፈት አለባትም ብሏል፡፡

ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢኒሼቲቭ (EITI) ÷ ኢትዮጵያ ያልተነካ ከ200 ሜትሪክ ቶን በላይ ወርቅ ፣ 366 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የድንጋይ ከሠል፣ 70 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የብረት ማዕድን ክምችት እንዳላትም ጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.