Fana: At a Speed of Life!

መላው የከተማችን ነዋሪዎች፤በአፍሪካዊነታችን እየኮራን ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት በጋራ እንቁም-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሚቀጥለው ሳምንት በመዲናዋ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
 
በአፍሪካዊነቴ እኮራለሁ !!
 
መላው የከተማችን ነዋሪዎች፤ በአፍሪካዊነታችን እየኮራን ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬት በጋራ እንቁም!!
 
የአፍሪካ ህብረት 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ ሊካሄድ ቀናት ብቻ ቀርተዉታል፡፡
 
ከተማችን አዲስ አበባ የአፍሪካዊያን መዲና ፤ የአለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል የህብረብሄዊነት አርማ ነች፡፡
 
ሃገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ለመላ አፍሪካውያን ድምፅ በመሆን በተደጋጋሚ ለአፍሪካውያንና ለፓን-አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ትልቁን መሪነት ሚና ስትጫወት የነበረች አፍሪካውያን የአሸናፊነት ተምሳሌት ነች፡፡
 
አፍሪካውያን ወደ ቤታቸው የሚሰበሰቡበት ይህ ጉባኤ ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀው በተለይም በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ብሎም ለከተማችን አዲስ አበባ ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡
 
ሃገራችን ኢትዮጵያ ገጥሟት ከነበረው ውስጣዊና ውጫዊ የህልውና ትግል አንፃር ጉባኤው ለኢትዮጵያ የመልካምና የአሸናፊነት ማብሰርያ ነው፡፡
 
በተደረገው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ፤አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም ከጎናችን መሆናቸውን ጉባኤው እንዲካሄድ በመወሰን ያሳዩበትና ፤ ለሃገራችን ያላቸውን አክብሮትና ወዳጅነት ያረጋገጡበትም ነው፡፡
 
ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም፤ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ሊታደሙባት ቀርቶ ፤ያሉትም የውጪ ዜጎች ከተማዋን ለቀው መውጣት አለባቸው በማለት በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄድብን የነበረውን የሚድያ ዘመቻ በማጋለጥ ፤ እውነትም ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም በራሷ ማረጋገጥ የምትችል መሆኗን፤ ከተማችን አዲስ አበባም ከምንጊዜውም በላይ ሰላማዊና ውብ እንደወትሮውም የአፍሪካውያን መዲና ሆና መቀጠል የሚያስችል ብቃት ያላት መሆኑን ያረጋገጠ ጭምር ነው፡፡
 
ጉባኤው ለከተማችንም ይሁን ለሃገራችን ሌሎችም ብዙ ትርጉሞች ያሉት ጉባኤ ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህ ጉባኤ ስኬታማነት ሁላችንም ትልቅ ሃላፊነት አለብን፡፡
 
ከተማችንም ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ በደመቀና ባማረ መልኩ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጋለች፡፡
 
መላው የከተማችን ነዋሪ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው ከተማ አቀፍ የፅዳት ፕሮግራም ላይ ያለማንም አስተባባሪና ያለማንም ቀስቃሽ በራሱ ወጥቶ አካባቢውንና ሰፈሩን እንዲያፀዳና እንዲያሳምር ጥሪዬን አቀርባለሁ።
 
ውድ ባለሃብቶቻችንም በየአካባቢው ህንፃዎችን እንድታሸበርቁና የውስጥና የውጪ መብራቶችን ባለማጥፋት ለከተማው ድምቀት የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ፡፡
 
በተጨማሪም በክፉ ቀን ከተማችንን በመታደግ ትልቅ ሚና የተወጣችሁ ህዝባዊ ሰራዊቶቻችን በየአካባቢው ሰላማችንን በመጠበቅ ፤ ባህላችንን ገፅታችንንና ህብረብሄራዊ ቀለማችንን በማስተዋወቅ ፤ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበርና ተጋግዞ በመስራት ይጠበቅባቹሀል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ከወጥሮው በተለየ ሁኔታ የሚጠበቅብንን ሁሉ ብቁ አገልግሎት በመስጠት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
 
በአጠቃላይ መላው የከተማችን ነዋሪ በተለመደ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት እንግዶቹን በማስተናገድ ወደ መዲናችን የሚመጡ አፍሪካውያን ወደ ቤታቸው እንደመጡ ሆኖ እንዲሰማቸው በማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እላለሁ !!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.