Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት እንደ አዲስ ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጠናው የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ክልላዊ መንግስት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት እንደ አዲስ ከወረራቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጣና በቀጠናው የከፈተውን ጦርነት እንዲያቆም የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሳሰበ።
 
የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።
 
አሸባሪው ህወሃት በአፋር ህዝብ ላይ ከሁለት አመት ተኩል በላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቢፈጽምበትም ለወንድም የትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በርካታ ስራዎች በክልሉ መንግስት በኩል መሰራታቸውን ነው መገለጫው ያመለከተው።
 
የክልሉ መንግስት ከተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሷል።
 
ነገር ግን በውሸት እና በሴራ አፉን የፈታው አሸባሪው ህወሃት በአፋር ኪልበቲ ረሱ /ዞን ሁለት/ በተለያያዩ ወረዳዎች ወሰን ጥሶ ገብቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ የከፈተውን ጦርነት አስመልክቶ መሰረተ ቢስ መግለጫ ማውጣቱን አስታውቋል።
 
እርስ በርሱ የሚጋጨውና በውሸቶች የታጨቀው የህወሃት መግለጫ የአፋርን እና የትግራይ ህዝቦችን በማጋጨት የማይረባ ትርፍን ለማጋበስ ቆርጦ እንደተነሳ በግልፅ ቃላቶች በማሳየት እና የአፋርን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት በሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን አመልክቷል።
 
ከአሁን በፊት በአፋር ክልል በርካታ ወረዳዎች ወሰን ጥሶ በመግባት በአሰ ዳ፣ በጋሊኮማኘ፣ በኡዋ፣ በጭፍራ፣ በሀደሌ ኤላ፣ በደርሳ ጊታ እና ሌሎች አካባቢዎች አሰቃቂ የዘር ማጥፋትን ጨምሮ በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን የሽብር ቡድኑ ማድረሱን አስታውሷል።
 
“ለሰላም ስል ወጥቻለሁ” የሚል የውሸት ማደናገሪያ ቢነዛም ወሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች እንዲወጣ ቢደረግም በማግስቱ ከታህሳስ 10 ቀን 2014 ጀምሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ እና ለመበቀል በኪልበቲ ረሱ በአብኣላ በኩል እና በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ግን ጥቃቶችን አቁሞ አያውቅም ብሏል።
 
ይህንንም የሽብር ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃቶች እንዲያቆም የክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ የቆየ ቢሆንም ቡድኑ ከባድ መሳሪያ ወደ ንፁሀን ዜጎች በመተኮስ ህይወት እየቀጠፈ እና ሆስፒታሎች፣ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ኢላማ ያደረገ የከባድ መሳሪያ ድብደባ እየፈፀመ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
 
ከሰሞኑ ደግሞ በተደራጀ መልኩ በአብአላ፣ በመጋሌና ኤረብቲ ወረዳዎችን በመቆጣጠር እና በራህሌ ወረዳንም ከፊል ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት ከባድ ጥቃት ከፍቶ ንፁሀንን በመግደል እና በማሳደድ ወረዳዎቹን እያወደመ እንደሚገኝና ከ220 ሺህ በላይ ንጹሃን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ የአፋር ክልል አስታውቋል።
 
አሸባሪው ቡድን መግለጫ ብሎ በሰጠው የውሸት ተረት ተረት ለአፋር እና ለትግራይ ህዝብ አሳቢ መስሎ የራሱን የሽብር ዕድሜውን ለማራዘም እና ህዝቦችን ለማባላት ባለፉት ሶስት አመታት ሲጠቀምበት የነበረ ሴራ በመሆኑ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የሽብር ቡድኑ የሚያሰራጫቸው የውሸት ፕሮፖጋንዳ እና ድራማዎች ሰለባ ሳይሆኑ ከወንድም የአፋር ህዝብ እና መንግስት ጎን በመሆን የትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና አፈና ጊዜውን ሊያሳጥር ይገባል ሲል አሳስቧል።
 
አሸባሪው ቡድን የራሱን እድሜ ከማራዘም ውጭ ጭራሽ ቅንጣት ታክል ለህዝብ ሰብአዊነት የሚሰማው አለመሆኑ የአፋር ንፁሃንን በመግደልና በማሸበር ብቻ ሳይሆን እየገለፀ ያለው፣ ከትግራይ እናቶች ጉያ መንጥቆ የሚያወጣቸውን በጦርነቱ በማሰለፍ እና በኪልበቲ ረሱ በኩል ለትግራይ ህዝብ ይደርስ የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈፀምም ነው ብሏል።
 
ቡድኑ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ እየፈጸመ ካለው የሽብር ተግባሩ እንዲወጣ የአለም ማህበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እና የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸውን የውሸት ማወናበጃ መግለጫዎችን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት ይህን ድርጊቱን በቃ እንዲል ጥሪ አቅርቧል።
 
በአካባቢው አንድም የመንግስት ሀይል በሌለበት እና “የኤርትራ ወታደሮች እና ቀይ ባህር አፋር” በሚል በሬ ወለደ ወሬ ሽፋን ንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲያቆም እና ገብቶ ከነበረባቸው የአፋር ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በአስቸኳይ እንዲያወጣ እንዲደረግ ክልል ጠይቋል።
 
የክልሉ መንግስትም ሆነ የአፋር ህዝብ ለትግራይ ህዝብ በቡድኑ ወረራና ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር የሚሰራ ይሆናልም ብሏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.