በቦረና ድርቅ ያስከተለውን ክፉ ጊዜ በቀደመው ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የመረዳዳት ባሕላችን ልናልፈው ይገባል ሲሉ የአገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቦረና ዞን ሕዝብ በድርቅ ምክንያት የመጣውን ክፉ ጊዜ በቀደመ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ ባሕሉ መሰረት ተረዳድቶና ተደጋግፎ እንዲያልፈው የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
የአገር ሽማግሌዎቹ የቦረና ሕዝብ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ በሚሰኝ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባሕሉ ደስታና ችግሩን ሲጋራ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።
በዞኑ የሁለት ወቅት ዝናብ ባለመጣሉ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ሃብት ብቻ ኑሮውን የሚመራውን አርብቶ አደር የሌሎችን ድጋፍ እንዲጠይቅ አስገድዶታል።
ድርቁ የበርካታ እንስሳትን ሕይወት እየቀጠፈ አርብቶ አደሩን ጥሪት እያሳጣውም ይገኛል።
የአገር ሽማግሌው ቦርቦር ቡሌ በቦረና ሕዝብ ዘንድ አንድ ሰው ሲቸገር ቁጭ ብሎ በመወያየት የሚያስፈልገውን ሁሉ በማዋጣት መርዳትና መደገፍ የተለመደ እንደሆነም አንስተዋል።
ሕዝቡ ጥንት ከአያት ቅድመ አያቶቹ ይዞት የመጣውን የመረዳዳት ባህል ዛሬም በማስቀጠል፥ አሁን በአካባቢው የደረሰውን የድርቅ አደጋ በመተጋገዝ ለማለፍ “አበክረን ልንሰራበት ይገባል” ብለዋል።
አሁንም በአካባቢው በጣም የተጎዱትን በባሕላችን መሰረት ልንረዳቸው ይገባልም ነው ያሉት።
የአገር ሽማግሌ ሊብን ጃተኒ በበኩላቸው፥ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም የሚታወቅበትን የመረዳዳት ባሕል ይበልጥ በማዳበር በችግር ላይ ከሚገኙ አርብቶ አደሮች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቦረና ለዘመናት የዘለቀውን የ’ቡሳ ጎኖፋ’ የመረዳዳት ባሕል በማስቀጠል የተሻለ ሁኔታ ላይ ያለው ይበልጥ የተቸገረውን አርብቶ አደር ሊረዳ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስትና ሌሎች አካላት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሕዝቡ ባለው ነገር ሁሉ እርስ በርሱ እንዲደጋገፍም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአገር ሽማግሌው ቦርቦር ቡሌ የተከሰተው ድርቅ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ አስከፊና እንስሳትን እየጨረሰ መሆኑን ጠቅሰው ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድርቅ ለተጎዱት ወገኖቹ ድጋፍ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።
የአገር ሽማግሌዎቹ መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ መጠን በማሳደግ ተደራሽ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!