ኢትዮጵያ በግማሽ ዓመቱ 39 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድርና እርዳታ ማግኘቷ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በ2012 ግማሽ በጀት ዓመት 39 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድርና እርዳታ ማግኘቷን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ብድሩ የተገኘው ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና ሀገራት መሆኑን አስታውቋል።
በዚህ መሰረትም 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብሩ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና በይነ መንግስታዊ ተቋማት የተገኘ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብሩ በብድር እና 13 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ደግሞ በእርዳታ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከመንግስታት ደግሞ 9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በብድር እንዲሁም 13 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በእርዳታ በአጠቃላይ 23 ነጥብ 2 ቢሊየን ብድርና እርዳታ ማግኘት እንደተቻለ ነው የተጠቆመው።
በሌላ በኩል በ2ዐ12 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና በይነ መንግስታዊ ተቋማት 29 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የውጭ ሃብት ፍሰት በብድርና እርዳታ ተገኝቷል።
እንዲሁም ከመንግስታት 25 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የውጭ ሃብት ፍሰት በብድርና እርዳታ መመዝገቡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በአጠቃላይ ከሁለቱ ምንጮች በግማሽ ዓመቱ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 28 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በብድር እና 25 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በእርዳታ በአጠቃላይ 54 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ፈሰስ ተደርጓል።