በመዲናዋ የደህንነት ካሜራዎችን ለመግጠም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ ) በአዲስ አበባ ከተማ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ የደህንነት ካሜራዎችን ለመግጠም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በዘርፉ ልምድ ካለው ድርጅት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ቴክኖሎጂውን መዘርጋት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
የዜጎችን ደህንነት በቴክኖሎጂ ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም በመዲናዋ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ የደህንነት ካሜራዎችን ለመግጠም እንቅስቃሴ መጀመሩን አንስተዋል።
የሚገጠሙት የደህንነት ካሜራዎች ወንጀልን ቀድሞ በመከላከል ዜጎች ደህንነት ተሰምቷቸው እንዲኖሩ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ ከተማዋ ሲገቡ የተሻለ ጥበቃን ለማድረግ እገዛው የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሚገጠሙት የደህንነት ካሜራዎች እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ምስል የመለየት አቅም ያላቸው መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡