የደቡብ ሱዳን መንግስት የሀገሪቱ ግዛቶች ቁጥር ከ32 ወደ 10 ዝቅ እንዲል ወሰነ
አዲስ አበባ፣የካቲት 7፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሀገሪቱ ግዛቶች ቁጥር ከ32 ወደ 10 ዝቅ እንዲል መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ በሀገሪቱ የተጀመረው የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት እውን ይሆን ዘንድ የክልሎችን ቁጥር ከ 32 ወደ 10 ዝቅ እንዲል መወሰኑን አስታውቀዋል።
ውሳኔው አሳዛኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሲባል ተቃዋሚዎችም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር እስካሁን በተደረሰው ውሳኔ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት አለመኖሩ በዘገባው ተመላክቷል።
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች በፈረንጆቹ 2018 በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚያስችል የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ተቀናቃኝ ሃይሎች የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደቱን ሲያራዝሙ ቆይተዋል።
በፈረንጆቹ ህዳር 2019 የአንድነት መንግስትን ለመመስረት ቢስማሙም ቀኑ ሲደርስ የጊዜ ገደቡን በ100 ቀናት ማራዘማቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ም አሜሪካ በከፍተኛ ባለስልጣናቱ ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወቃል።
ኢጋድ በቅርብ ባደረገው ስብሰባም ሱዳን የአንድነት መንግስቱን ለመመስረት ሊኖሯት ስለሚገባቸው ክልሎች ብዛት እስከ ቅዳሜ ድረስ መፍትሄ እንድታስቀምጥ አቅጣጫ አስቀምጠው ነበር።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፥ የደቡብ ሱዳን የፓለቲካ ሃይሎች የደረሱበትን የሽግግር መንግስት ምስረታ ሳያራዝሙ ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል ።
በደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ ከ2013 ጀምሮ በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ፥4 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ምንጭ፡-አልጀዚራ እና ሬውተርስ