በአውሮፓ በኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያው ሰው ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ በኮሮና ቫይረስ በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ሰው ህይወት ማለፉ ተሰምቷል።
በፈረንሳይ ህይወታቸው ያለፉት የ80 ዓመቷ አዛውንት ለጉብኝት ከቻና ሁቤይ ግዛት የመጡ መሆናቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህም ከእስያ ሀገራት ውጪ በቫይረሱ ምክንያት የተመዘገበ የመጀመሪያው ሞት መሆኑ ነው የተገለጸው።
በቅርቡ በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና በሽታ አድማሱን በማስፋት በተለየዩ የዓለም ሀገራት ውስጥ እየተዛመተ ይገኛል።
አሁን ላይ በቻይና ብቻ ከ1ሺህ 500 በላይ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸው ተገልጿል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ 66 ሺህ 492 ማሻቀቡን የቻይና ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረ የመጀመሪያው ሰው በግብፅ ውስጥ መገኘቱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
በቫይረሱ እንደተያዘ የተጠረጠረው ግለሰብ የውጭ ሀገር ዜጋ ሲሆን፥ በአሁኑ ሰዓትም ተገቢው የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑ በዘገባወ ተመላክቷል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ