82 ከመቶ የሚደርሱ የህዝበ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መተግበሪያዎች የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑ ጥናት አመላከተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 82 ከመቶ የሚሆኑ የህዝበ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚጠቀሙባቸዉ መተግበሪያዎች የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት እንዳለባቸው ጥናት አመላከተ፡፡
ከአምስት የህዝብ አግልግሎት ሰጪዎች ከሚጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች መካከል ከአራት በላይ የሚሆኑት ማለትም 82 በመቶ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት እንዳለባቸዉ የቬራኮድ ጥናት ይፋ አደረገ።
ይህ ተጋላጨነት መጠን ከሌሎች ሴክተሮች አንጻር በጣም ከፍተኛዉ የሚባል የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መሆኑን በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ የተሰማራዉ “ቬራኮድ” ኩባንያ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡
ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲነጻጸር በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ሴክተሮች ጥቅም ላይ የዋሉ መተግበሪያዎች ላይ የተገኙ ክፍተቶችን ለመጠገን በእጥፍ የመጠገኛ ጊዜ እንደሚጠይቅ ነዉ ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት።
የቬራኮድ ዋና የምርምር ኦፊሰር የሆኑት ክሪስ ኢንግ፣ በህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በሃላፊነት ያሉ እና ፖሊሲ የሚያወጡ አካላት ጊዜያቸዉ ያለፈባቸዉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ከፍተኛ የህዝብ ሚስጠራዊ መረጃ የያዙ መተግበሪያዎች በመረጃ መዝባሪዎች ቀዳሚ ኢላማ መሆናቸዉን ሊገነዘቡ እና የማስተካከያ ርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ማለታቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።