11 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዲያዙ ማድረጉን ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዲያዙ ማድረጉን ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ባካሄደው ማጠቃለያ ግምገማ ችግሮችን በመፈተሽ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና በእጥረት የተለዩትን ለማረም የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል።
በማጠቃለያ ግምገማው ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ የሀገሪቱን ህግና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ማስከበር ተቀዳሚው ተግባራችን ነው ብለዋል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎችን ህልም በማክሸፍና ሀገርን በማፅናት በኩል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
ትላልቅ የሀገር ሀብት የሆኑ መሰረተ ልማቶችንና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ተቋማትን በመጠበቅ እንዲሁም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረግ ስኬታማ ሥራ መሰራቱንም ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዲያዙ መደረጉን ማንሳታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪም የጦር መሣሪያ፣ የአደገኛ ዕፅ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎችን በመቆጣጠር በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ትልልቅ ዘመቻዎች አመራሩና አባሉ ህይወቱን ገብሮ የሠራቸው ሥራዎች አሁን ላለንበት ደረጃ እንድንደርስ አድርገውናል ብለዋል።