Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተቀበሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ።

የኖቤል የሰላም ሽልማት ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በኖርዌይ ኦስሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ባለፈው መስከረም 30 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ዶክተር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ሁሉም ባለደርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፀኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።

የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለረጅም አመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሀሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።

ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን በመካሄድ የሀገሪቱ ዜጎች ለተሻለ ህይወት ተስፋ እንዲያደርጉ አድርገዋል ብሏል ኮሚቴው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.