Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ኢትዮጵያ ስሟና ታሪኳ በዓለም አደባባይ ዳግም ከፍ እንዲል ያደረገ ነው-ጠ/ሚ ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያገኙት የኖቤል የሰላም ሽልማት ኢትዮጵያ ስሟና ታሪኳ በዓለም አደባባይ ዳግም ከፍ ብሎ እንዲታይ ያስቻለ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈትቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያገኙቱን 2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት እና በነገው ዕለት የሚደረግላቸውን አቀባበል አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያገኙት የኖቤል የሰላም ሽልማት ዓለም ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተው ሽልማትም የኢትዮጵያዊያን ብሎም የመላው አፍሪካውያን መሆኑን አውስተዋል።

የተገኘው ሽልማት እስከአሁን ድረስ በሀገር ውስጥ እና በቀጠናው ለተሰሩ ስራዎች እውቅና የሰጠ ብቻ ሳይሆን ነገም ለሚሰሩ ስራዎች አደራ መሆኑንም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነገው ዕለት አዲስ አበባ ሲገቡም ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

በዚህ አቀባበል ላይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎ እንደሚሳተፉ የገለጹት ሃላፊው፥በትምህርት ቤቶች እና በስራ ቦታዎች እውቅና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደራሳቸው ሁኔታ ለስኬቱ እውቅና የሚሰጡበት መንገድ ማመቻቸት ይችላሉ ተብሏል።

በመግለጫው እውቅና የመስጠት ስነ ስርዓቱ ስለ ሰላም ፣ ፍቅር እና አብሮነት መልዕክት የሚተላለፍበትም እንደሚሆን ተነግሯል።

እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ ጥላቻ ፣ ቂም እና ቁርሾ ለማስወገድ ዳግም ቃል የሚገባበት እንደሚሆን ተመላክቷል።

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.