Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከአሜሪካ አቻቸው ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ ዋሽንግተን በሚገኘው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባካሄዱት ውይይት በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በዚህ ወቅትም አቶ ገዱ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ባለው ለውጥ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መስፈን አሜሪካ እያደረገች ላለው ድጋፍ ኢትዮጵያ ግምት እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ መስክ ለሚደረገው ሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት የለውጥ ጉዞ እና በተቋማት ግንባታ ረገድ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ውይይት በውጤት እንዲቋጭ እና በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ ጥረቷን እንደምትገፋበት የገለጹት አቶ ገዱ፥ ለዚህ ስኬት የአሜሪካ አጋርነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ህዳሴ ግድቡ ጋር ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ሳይሆን የህዝቦቿን የዘመናት የልማት ጥያቄ ለመመለስ የምትገነባው ሀገራዊ ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጸዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማታቸውን በመቀበላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ይህም ለጀመሩት የለውጥ ጉዞ ተጨማሪ አቅም ይፈጥርላቸዋል ነው ያሉት።

አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንደምትደግፍ እና በተለይም የአሜሪካ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ግፊት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት የተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥና የኢንቨስትመንት ስራ ምቹነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ከቀጠናው ሰላምና መረጋጋት አኳያ በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጉዳይ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መስተጋብር አጠናክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ልዩነታቸውን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ የሀገራቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ለዚህም ድጋፏ ይቀጥላል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.