Fana: At a Speed of Life!

ታህሳስ 10 ቀን ወደ ህዋ ለምትመጥቀው ሳተላይት ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢቲ አር ኤስ ኤስ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሳተላይት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ ስትመጥቅ በዕለቱ የሚኖሩ መርሃ ግብሮች ይፋ ተደርገዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲቲዩት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሳተላይቷ ታህሳስ 10 ቀን ከማለዳው 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ስትመጥቅ ህዝቡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መመልከት ይችላል ተብሏል።

ታይዋን ውስጥ ከሚገኝ ማዕከል የምትመጥቀው ሳተላይት በምትመጥቅበት ወቅት የሚኖረው የአየር ንብረትም በትንበያ ደረጃ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከስፔስ ሳይንስ ኢንቲቲዩት እና ከጋዜጠኞች የተውጣጣ የልዑክ ቡድንም ሁነቱን ለመከታተል ወደ ስፍራው የሚያመራ ይሆናል።

የሳተላይት መቆጣጠሪያ በሚገኝበት እንጦጦም በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያዩ አካላት ተገኝተው የሳተላይቷን መምጠቅ ይከታተላሉም ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም በመስቀል አደባባይ ደግሞ የሳተላይቷን ቅርጽ የሚመስል ግዙፍ ማሳያ የተዘጋጀ ሲሆን ከማለዳው 3 ሰዓት ጀምሮ ለህዝብ ክፍት ይሆናል ተብሏል።

በመለሰ ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.