Fana: At a Speed of Life!

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ራፖርተር የሚመራው ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝት ዋና ዋና ግኝቶችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በልዩ ራፖርተር ዳቪድ ካየ የሚመራው የልዑካን ቡድን ከአንድ
ሳምንታት በላይ በኢትዮጵያ ከበርካታ የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር በሚዲያና በአጠቃላይ ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር የተያያዙ የዴሞክራሲ መብቶች ዙሪያ ከጠቅላይ አቃቤ ህግና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ጥናቶችን ሲያካሂድ እንደቆየ በመግለፅ ዋና ዋና ያላቸውን ግኝቶች ዛሬ ይፋ አደረገ።

በዚሁ መሰረት መንግስት እያካሔደው ያለው መጠነ ሰፊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጥ የሚበረታታና ወደፊት ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጥል እንደሆነ አንስቷል።

ሃገሪቱ አዲስ በምታወጣቸው ህጎች በተለይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ሙያተኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ሌሎች አካላትን በአማካሪነት፣ ህግ በማርቀቅና በፍትህ ሂደት እያደረገ ያለው አሳታፊነት የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል።

የሕግ፣ የፍትሕ፣ የሲቪክ ማህበራት ኤጄንሲ፣ የኢኖቬሽንና የሚዲያ ተቋማት በሙያተኞች እንዲመሩ መደረጉ ለውጡን ለማስቀጠል ከተቋሞቹ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑንም በሪፖርቱ አብራርቷል።

በሃገሪቱ ያለውን የኢንተርኔትና የሞባይል ኔትዎርክ ተደራሽነት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ለማሳደግ የተያዘው እቅድ የኢንፎርሜሽን ተደራሽነትንና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥን በመሆኑ የመንግስትን ቁርጠኝነትና የለጋሽ ሃገራትን ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑንም በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

ምንም እንኳን መንግስት ከአሁን በፊት የነበረውን የጸረ ሽብር አዋጅ ለመቀየር ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ ቢሆንም አዲሱ አዋጅ ጸድቆ የቀድሞውን አዋጅ መቀየር ባለመቻሉ አንዳንድ ቅሬታዎችና መኖራቸውን የጠቆመ ሲሆን፥ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኩል በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የማስተካከያ ሃሳቦችን በመስጠት በልዩ ራፖርተሩ የተሰጡ አስተያየቶችን በማስተካከል በቀጣይ መንግስት የያዘውን ማሻሻያ ለማስፋት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን እንደገለፀ ነው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.