Fana: At a Speed of Life!

ግብፅ ኳታርን የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረትን በመደገፍ ወነጀለች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ ኳታርን የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረትን ትደግፋለች ስትል ከሳለች።

ኳታር በግብፅ መንግስት በአሸባሪነት ለተፈረጀው የሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት የተለያዩ ድጋፎችን እንደምታደርግ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የግብፅ ተወካይ አምጋድ አብደል ጋፋር አስታውቀዋል።

ተወካዩ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ኳታር በባህረ ሰላጤው ለሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን ድጋፍ በማድረግ የቀጠናውን አለመረጋጋት እያባባሰች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በባህረ ሰላጤው የሚንቀሳቀሱ እና ለግብፅ አደገኛ የሆኑ የሽብር ቡድኖችን በመደገፍ የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ እየሰራች ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በቀጠናው የአይ ኤስ እና አል ቃይዳን አስተሳሰብ ለማስረፅ በርካታ ስራዎችን ስታከናውን መቆየቷን የገለጹት ተወካዩ፥ አሁን ላይም ለሙስሊም ወንድማማቾች ህብረት ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

ይህም የሀገሪቱ መንግስት በግብፅ ብሎም በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከመፈለጉ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም ኳታር በግብፅ እና በአካባቢው ሀገራት ሽብርተኝነት ለማስፋፋት የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም አሳስበዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2017 ሰኔ ወር ላይ ጀምሮ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ባህሪን ኳታር በቀጠናው ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል  ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸው ይታወሳል ።

ምንጭ፦ ሚድል ኢስት ሞኒተር

You might also like
Comments
Loading...