Fana: At a Speed of Life!

የዲላ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23 ፣2012 (ኤፍ.ቢ. ሲ) የዲላ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን የህክምና መስጫ ቦታ ችግር ለመቅረፍ ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡
 
ሆስፒታሉ የጌዴኦ ዞንን ጨምሮ ለሲዳማ ዞን አጎራባች ወረዳዎች፣ ለአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች፣ ኦሮሚያ ክልል ጉጂና ቦረና ዞኖች ለሚኖሩ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
 
በዚህም ምክንያት ሆስፒታሉ የህክምና መስጫ ቦታ ችግር አለበት ያሉት የሪፈራል ሆስፒታሉ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የቦርድ ሰባሳቢ ዶክተር ዮናስ ሰንደባ ይህን ችግር ለመቅረፍና የአገልግሎት ጥራትና ብቃቱን ለማሳደግ 894 ሚሊየን ብር በሚሆን ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
 
የግንባታው አፈጻጸምም 84 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸው በያዝነው አመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
 
ሪፈራል ሆስፒታሉ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዋና ዋና የሚባሉ የጤና ፕሮግራሞችን የሚሰጥ ሲሆን በሀገሪቱ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን በማስመረቅ ረገድ የጎላ ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
 
ሪፈራል ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው የመደበኛ የህክምና አገልግሎቶች በተጨማሪ የአይን ህክምና ማዕከል በመገንባት ከኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በዞኑና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
 
የዲላ ሪፈራል ሆስፒታል የአጥንት ስብራት ህክምናን ጨምሮ በደቡብ ክልል ሁለት ቦታ ብቻ የሚሰጠውን መድሀኒት የተላመደ የቲቢ ህክምናና የፆታ ጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶች ነፃ ህክምና እየሰጠ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
 
ሌሎች ዘመናዊ ህክምናዎችን ለመስጠት በያዝነው አመት የሲቲ ስካን ማሽን አስገብቶ አገልግሎት ለመጀመርና የካርድ ክፍል አገልግሎትን በኮምፒውተር የታገዘ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
 
እንዲሁም የኩላሊት እጥበት እና የፌዝዮቴራፒ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የሪፈራል ሆስፒታሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶተር ሰላማዊት አየለ መግለፃቸውን ከክልሉ የመንግስት ኮሙኔኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
You might also like
Comments
Loading...