Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲጠቀምበት የነበረውን አርማ አሻሻለ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለረዥም አመታት ሲጠቀምበት የነበረውን አርማ አሻሻለ።

ትናንት 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው ፌዴሬሽኑ በጉባኤው ፌዴሬሽኑን አይገልጽም እንዲሁም አላስፈላጊ ምልክቶች ተካተውበታል በሚል ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየውን አርማ አሻሽሏል።

በዚህም በአርማው መካከል የነበረው የሰብል ምስልና የአዲዳስ ምልክት ያለበት መጫወቻ ኳስ ተነስተው በአዲስ መልክ ተስተካክሏል።

በተጨማሪም በጉባዔው በተጓደሉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ አዲስ አባላትን መምረጥ፥ የዲሲፒሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም አዋቅሯል።

በጉባኤው ወቅት በቀረበ ሪፖርት ፌዴሬሽኑ በገቢ ራሱን ለመቻል እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው አመት ከ201 ሚሊየን ብር በላይ ያልተጣራ ገቢ ያገኘ ሲሆን፥ ከ83 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ፌዴሬሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል።

በውድድሮች ወቅት የሚታየው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እና የበጀት እጥረት በበጀት አመቱ የተነሱ ፈተናዎች እንደነበሩ በሪፖርቱ ተካቷል።

በውይይቱ መጨረሻም ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ ሀዋሳ ከተማ ላይ እንዲደረግ ወስኖ ጉባዔው ተጠናቋል።

በሱራፌል ደረጄ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.