Fana: At a Speed of Life!

ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መንግስታቸው እንደሚሰራ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23 ፣2012 (ኤፍ.ቢ. ሲ) የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያውያን በኬንያ እንደ ሀገራቸው ሰርተው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መንግስታቸው እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
 
ኡሁሩ ኬንያታ ከኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የዲጎድያ ማህበረሰብ ንጉስ አብዲሌ የተመራውን የልዑካን ቡድን በብሄራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
 
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በዚህ ወቅት ÷ ባለፉት 40 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኬንያ የመጡ ኢትዮጵያውያን ሠላማዊ ኑሮ እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ከኬንያውያን ጋር አንድ በመሆን ሃብት አፍርተው ቤተሰብ መስርተው በመኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ይህም እንዲቀጥል እንደሚሰሩም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጎረቤቶቻችን ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖር እንሰራለን ሲሉ መናገራቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
ከኬንያ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲው ለሚያደርገው ጥረት ፕሬዚዳንቱ አመስግነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር መፅሃፍ ናይሮቢ በመመረቁ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡
 
በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው÷ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኬንያውያን እና መንግስታቸው ለሚያሳዩት ፍቅር እና ክብር አመስግነው የኬንያውያን አንድነት እና ዕድገት ለማረጋገጥ የተዘጋጀው የህብረት ሰነድ ይፋ በመሆኑም ለፕሬዚዳንቱን የ ደስታ መልክት አስተላልፈዋል፡፡
You might also like
Comments
Loading...