Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ ከጀርመን ልኡካን ቡድን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ የጀርመን ፓርላማ አባል ከሆኑት ሄርማን ግሮሄ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው አምባሳደር ማርቆስ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ስላለው ፖለቲካዊና የኢኮኖሚያዊ ለውጥ ዙሪያ በሄርማን ለተመራው የልዑካን ቡድን ገለፃ አድርገዋል።

ሁሉን አቀፍ ማሻሻያዎችና ለውጦች በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ሚኒስትር ዲኤታው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጠናው ሀገራት አካባቢ በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በኢኮኖሚ ትስስር ጉዳዮች ዙሪያ እየሰራች ያለውን ስራ በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል።

ሄርማን ግሮሄ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

የጀርመን ባለሃብቶች አሁን ካለው በተሻለ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው እና ይህንኑ ለማፋጠን በሀገራቱ መካከል ተከታታይ ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካዊ ትብበር መስክ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የጀርመን ገለልተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት የመክፈት ፍላጎት እንዳለውም ጠቁመዋል።

 

You might also like
Comments
Loading...