Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ ከተመድ የመናገር ነጻነት ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22 ፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመናገር ነጻነት ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ካዬ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ።

የውይይት መድረኩን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስና ባልደረቦቻቸው ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በበኩላቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እየተካሄዱ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ መሰረትም ለውጡን ተከትሎ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ መደረጉ፣ የሚዲያ ነፃነት ያለገደብ እንዲስፋፋ መደረጉና በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱት እርምጃዎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት እንድታገኝ ማድረጉን አብራርተዋል።

የልዑካን ቡድኑ መሪ ዴቪድ ካዬ በበኩላቸው በበርካታ ሀገራት በተመሳሳይ አጀንዳ ዙሪያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልፀው፥ በዛሬው ዕለት የተደረገላቸው ገለፃ ለየት ያለና ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ፅንሰ ሀሳብና አተገባበር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሆነና ለዚህ መልካም ውጤት ኢትዮጵያ የተመድ ድጋፍ እንደማይለያት አረጋግጠዋል።

በዴቪድ ካዬ የሚመራው የልዑካን ቡድን በሚቀጥሉት ቀናትም ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከተለያዩ የሲቪክ ተቋማት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከስራ ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።

You might also like
Comments
Loading...