Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በፈረንሳይ የተወሰኑ ምርቶች ላይ 100 ፐርሰንት ቀረጥ ልትጥል ነው

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በፈረንሳይ የተወሰኑ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል መሆኑን አስታወቀች።

የሃገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ፈረንሳይ ወደ አሜሪካ በምታስገባቸው የሻምፓኝ፣ አይብ፣ የእጅ ቦርሳ እና ውድ መዋቢያ ምርቶችን ጨምሮ፥ በሌሎች የተወሰኑ ምርቶች ላይ ዋሽንግተን 100 ፐርሰንት ቀረጥ እንደምትጥል አስታውቋል።

ፈረንሳይ በቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ምርቶች ላይ የምትጥለው  አዲስ የቀረጥ ስርአት የአሜሪካን ኩባንያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ መሆኑ ለእርምጃው ምክንያት መሆኑንም ገልጿል።

ሚኒስቴሩ የፈረንሳይ አዲሱ ቀረጥ አሁን በስራ ላይ ካለው የቀረጥ ስርአት ጋር የሚጣረስና አለም አቀፉን ህግ የሚጥስ ነው ብሏል።

ከዚህ ባለፈም እንደ ጎግል፣ ፌስቡክ፣ አማዞን እና አፕል ባሉ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር መሆኑን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ÷  አዲሱ ስርአት የአሜሪካ ኩባንያዎችን ኢላማ ያደረገ ነው ሲልም ኮንኗል።

ይህን ተከትሎም ለዚህ ምላሽ በሚመስል መልኩ በፈረንሳይ በርካታ ውድ ምርቶች ላይ እጥፍ ቀረጥ እንደሚጥል ነው ያስታወቀው።

ፈረንሳይ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ተጨማሪ ቀረጥ የሚጣልባቸው ምርቶች 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ናቸው።

አዲስ ይጣላል ከተባለው ተጨማሪ ቀረጥ ጋር በተያያዘ የህዝብ አስተያየት እንደሚሰበስብም ጠቅሷል።

ፈረንሳይ ከሌሎች ሃገራት በሚገቡ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ምርቶች ላይ አዲስ የ3 በመቶ ቀረጥ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።

You might also like
Comments
Loading...