Fana: At a Speed of Life!

ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በሪፎርም ስራዎች ስያሜን ከመቀየር ጀምሮ ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እያካሄደ ያለው ሪፎርም ተልዕኮውንና የስራ ባህሪውን ግምት ውስጥ በማስገባት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ፕሮፌሽናል ተቋም በመመስረት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል የተቋሙን የ100 ቀን እቅድ አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ባካሄደው የሪፎርም ስራ ተቋሙን እንደገና ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አጠናቋል ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ አሁን ያለው የተቋሙ ስያሜ በአዲስ ይቀየራል ያሉት ሲሆን አዋጁን መነሻ በማድረግም ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች እንደ አዲስ መቀረፁ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚመራበት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማጠናቀቁን ኮሚሽነር ደመላሽ ተናግረዋል፡፡

ስትራቲጂክ ዕቅዱ ተቋሙ ከፖለቲካ ገለልተኛ፣ ብሄራዊ ጥቅምን እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብር ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮፌሽናል የመረጃ ተቋም እንዲሆን አቅጣጫ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶች ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች ሰነዶች ጭምር በሪፎርም ሂደቱ ተዘጋጅተው በተለያየ ደረጃ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ባለፉት ወራት ተልዕኮውን የሚመጥንና ከታወቁ ዓለም አቀፍ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርገው አሰራርና አደረጃጀት ከመፍጠር አንፃርም በርካታ ስራዎች በሪፎርም ማዕቀፍ ስራ ተከናውነዋል ነው የተባለው፡፡

ለአብነትም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ስጋቶችንና ሊፈጸሙ የሚችሉ አሻጥሮችን እንዲሁም ከባድ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈለጊ መረጃዎች ለሚመለከተው አካል የሚያቀርብ የኢኮኖሚ ደህንነት ዋና መመሪያ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽነሩ ሙያዊ ብቃትን ፣ የትምህርት ውጤትንና ስነ-ምግባርን እንዲሁም የብሄርና የፆታ ስብጥርን ግምት ውስጥ በማስገባት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንን በመመልመልና በመረጃ ኪነሙያ በማስልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ተግባራት በሪፎርሙ እንደተከናወኑ ገልፀዋል፡፡

የሰው ሀይል አቅምን ከማሳደግ አንፃር ሰራተኞች በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ስልጠናዎችንና የትምህርት ዕድሎችን አግኝተዋልም ተብሏል፡፡

በቀጣይ ለሰው ሀይል አቅም ግንባታ ትኩረት በመስጠትም ቀድሞ የነበረውን የስልጠና ተቋም በከፍተኛ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ፕሮግራሞቹን በማስገምገም በኮሌጅ ደረጃ በማሳደግ የብሄራዊ የመረጃ ኮሌጅ በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ እና ወደ ስራም እንዲገባ መደረጉ ተብራርቷል፡፡

ኮሌጁ በቀጣይ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ በተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም ለማደራጀት ልምድና አቅሙ ካላቸው አቻ አለም አቀፍ የመረጃ ተቋማት ጋር በተደረሰ ስምምነት በርካታ ስራዎች እና አቅሞች እየተፈጠሩ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

የተቋሙን የሪፎርም ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ባለፈው ወር ከአመራሮችና ከሰራተኞች ጋር ጥልቅ ውይይቶችና ግምገማዎች እንደተደረጉ ታውቋል፡፡

በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስምሪት የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩት የማበረታቻ እንዲሁም የስነ ምግባር ችግር የታየባቸውን ግለሰቦች ከስራ የማገድ፣ ጉዳያቸውም በህግ አግባብ እንዲታይ የማድረግና በሌሎችም ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደተወሰዱ ተጠቁሟል፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ሪፎርሙን ተከትሎ በሁሉም ዘርፎች ያመጣቸውን ውጤቶች በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ሁሉንም ዜጎች በፍትሃዊነት የሚያገለግል የመረጃ ተቋም ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ህዝቡ በባለቤትነት ከተቋሙ ጎኑ እንዲቆም ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ተቋሙ የሪፎርም ስራዎችን ያከናወነው ከሃገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምንጭ እንዳይሆኑና የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትሉ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለመንግስት ውሳኔ በግብአትነት እንዲውሉ ከማድረግ ባሻገር በአለም አቀፍ ደረጃና በቀጣናው ስጋት የሆነው ሽብርተኝነት በአገሪቱ ላይ ደቀኖት የነበረውን አደጋ በማስቀረት ረገድ ተቋማዊ ተልእኮውን እንደተወጣ ተገልጿል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.