Fana: At a Speed of Life!

በሀዋሳ በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋለው የመድሃኒትና ህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት ፈጥሯል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለው የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት መፍጠሩ ተገልጿል።

በከተማዋ የተለያዩ ጤና ተቋማት እያገለገሉ የሚገኙ ባለሞያዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥በጤና ተቋማቱ ላይ በስፋት የሚስተዋለው ይህ ችግር በተማሩት ልክ ማህበረሰቡን እንዳያገለግሉ ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማው ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ቡሪሶ ቡልዓሾ በበኩላቸው፥ በተለያየ ጊዜ የተጠየቁት የመድሃኒት አይነቶች በሚፈለገው ደረጃ እና ጊዜ አለማግኘት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም ከዓመታት በፊት የተከፈለባቸው የህክምና ቁሳቁሶች እና መድሃኒቶች ሃዋሳ በሚገኘው  የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ባለመድረሱ የተፈጠረ መሆኑን ነው ያብራሩት ።

ችግሮቹ በከተማዋ ዓመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው፥ በዘርፉ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው ሲነሱ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የደቡብ ክላስተር አስተባባሪ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ ዘመን ለገሠ፥ ችግሮቹ በማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ በግዥ ስርዓት አለመዘመን፣ በአደረጃጀት እና ዶላር እጥረት ምክንያት የተፈጠሩ መሆናቸውን አንስተዋል ።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ በተወሰዱ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች አቅርቦቱ መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ ይበልጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ፈጣን ለውጥ አምጪ እቅድ ተነድፎ እተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።

 

አፈወርቅ አለሙ

 

You might also like
Comments
Loading...