Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባህር ዳር ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ወይዘሮ ወርቅስሙ ማሞ በክልሉ ባለፉት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አንስተዋል፡፡

አፈ ጉባዔዋ በዋናነት የህግ የበላይነትን በማስከበር፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሰላም የመኖር ተግባራትን በማጠናከር በሃገራችን የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ እንደ ክልል ለመከላከል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እና የስራ ዕድልን ለመፍጠር፣ የግብርና ስራን ለማሳደግ እና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የ2012 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፓርት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸው በ2012 በጀት ዓመት የመኸር ሰብል ምርትን በ17 ነጥብ 3 በመቶ በማሳደግ 120 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ማድረስና ምርታማነቱንም በሄክታር ከ22 ነጥብ 8 ኩንታል ወደ 27 ኩንታል ምርት በሄክታር መሬት ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በተመሣሣይ የ2012/2013 የመኸር እርሻ ስራ 127 ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ለማምረት መታቀዱንና እቅዱ ለማሣካት የግብርና ግብዓት መቅረቡን አመላክተዋል፡፡

በዚህም በምርት ዘመኑ 6 ነጥብ 56 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ሪፓርቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ 4 ነጥብ 98 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 871 ሺህ 389 ኩንታል ጭማሪ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ 724 ሺህ 342 ስራ ፈላጊ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድ እንደተፈጠረላቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

ከመሠረተ ልማት አኳያ የክልሉን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን በበጀት ዓመቱ 75 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 77 ነጥብ 68 ማሳደግ እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

በማህበራዊ ዘርፍ የእናቶች ጤና አገልግሎት 611 ሺህ 491 እናቶች የቅድመ ክትትልና 406 ሺህ 848 እናቶች ቅድመ ወሊድ አገልገሎት መሠጠቱም ተነስቷል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ከ12 ሚሊየን 208 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰቡም ነው የተነሳው፡፡

ከፖለቲካና ፀጥታ አንፃር ደግሞ ክልሉን ሰላማዊና ከፀጥታ ስጋት ነፃ በማድረግ በኩል በሁሉም ቦታዎች የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በመሠራቱ አመርቂ ውጤት መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡

በዚህም በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 215 ሰዎች ምህረት ሲደረግላቸው፣ 405 ሰዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እጅ ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም 686 የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በሀይል እጅ እንዲሰጡ በማድረግ ህግና ስርአት የማስከበር ስራ መሠራቱን አቶ ተመስገን በሪፖርቱ አቅርበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለት ቀን ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር እና ሹመቶችን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡

ምክር ቤቱ በሁለት ቀን ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር እና ሹመቶችን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡

በለይኩን ዓለም እና በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.