Fana: At a Speed of Life!

ምርት ገበያው 7 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 131 ሺህ ቶን ምርቶችን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አገበያየ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 7 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 131 ሺህ ቶን ምርቶችን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ  በሩብ ዓመቱ 79 ሺህ 202 ቶን ቡና በ5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ሲገበያይ፥ 25 ሺህ 882 ቶን አኩሪ አተር ደግሞ በ396 ሚሊየን ብር ማገበያየቱን አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም 14 ሺህ 926 ቶን ሰሊጥ በ835 ሚሊየን ብር እንዲሁም 4 ሺህ 9 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ83 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል።

አፈጻጸሙ የዕቅዱን በመጠን በ140 በመቶ እንዲሁም በዋጋ ደግሞ በ145 በመቶ ያሳካ ሲሆን፥ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ86 እንዲሁም በዋጋ የ70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በሩብ አመቱ የቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ግብይት የተጀመረ ሲሆን፥ 7 ሺህ 65 ኩንታል አረንጓዴ ማሾ በ216 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል።

በቀጣይም ኑግን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ  ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ምርት ገበያው በክልል የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ያገበያየ ሲሆን፥ በሩብ አመቱ በሀዋሳ ኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል 25 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው 314 ሜትሪክ ቶን ቡና፣ በሁመራ ኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል 26 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 443 ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ማገበያየት ተችሏል ነው ያለው።

ቀጣዩ ሩብ ዓመት የምርት ወቅት በመሆኑ ምርት ገበያው ባሉት ቅርንጫፎች አዳዲስ ምርቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጸው።

አሁን ላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በምርት ገበያው መጋዘኖች በማከማቸት ከባንክ ብድር የሚያገኙበትን አሰራር  ለመዘርጋት ጥናት አድርጎ ማጠናቀቁን የገለፀው ምርት ገበያው፥ በሙከራ ደረጃ በበቆሎ ምርት በቡሬና በነቀምቴ የምርት ገበያው ቅርንጫች ለመተግበር የዝግጅት ሥራ እያከናወኑ ነው ብሏል።

እንዲሁም በተያዘው በጀት ዓመት አርሶ አደሩ፣ አቅራቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የግብይት መረጃ ማግኘት ማግኘት የሚችሉባቸው፥ 66 የገበያ መረጃ ማሰራጫ ኪዮስኮች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተተክለዋል።

የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ርክክብ ሂደትን የተቀላጠፈ ለማድረግም ለምርት መያዣነት የሚያገለግለውን ማሸጊያ ከ100 ኪሎ ግራም ወደ 50 ኪሎ ግራም እንዲቀንስ ማድረጉን ምርት ገበያው በመግለጫው አመላክቷል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.