Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የቀጨኔ ወላጅ አልባ ማዕከልን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የቀጨኔ ወላጅ አልባ ማዕከል በመገኘት የስራ እንቅስቃሴውን ጎብኝተዋል።

በወቅቱም በማዕከሉ ከሚገኙት ልጆችና ድጋፍና ክትትል ከሚያደርጉት ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም በተለይም ለልጆቹ አንድ ለአንድ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ የሚሰጡ ግለሰቦችን ማብዛት የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ሀሳባቸውን አንጸባርቀዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በውይይታቸው፥ የቀጨኔ ወላጅ አልባ ህጻናት ማዕከል የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደሚያደንቁ ገልፀዋል።

እንዲሁም ዜጎች በሀገሪቱ ውስጥ ድጋፍ የሚፈልጉ እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ህጻናትን እንዲንከባከቡ እና የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ልጆቹ አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው እና ማዕከሉን ለቅው ሲወጡ ለችግር እንዳይጋለጡ የሙያ እና ሌሎች የስራ ዕድሎች የሚመቻቹበት ሁኔታ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግም ማዕከሉ ልጆቹ በተለያዩ የስራ እድሎች ውስጥ እንዲታቀፉ የሚያስችሉ ጥረቶችን ጀምሯል ከነዚህ መካከል የደሮ እርባታ፣ የፀጉር ሙያ እና ሌሎቹም ይገኙበታል።

የማእከሉ አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው ምንም እንኳን የልጆቹ የምግብ፣ የመጠለያ እና የአልባሳትን ፍላጎት ማሟላት የተቻለ ቢሆንም ከዚህ ባለፈ የስነ ልቦና ድጋፍ መስጠት ላይ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሚችሉት ሁሉ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የቀጨኔ ወላጅ አልባ ማዕከል ላለፉት በርካታ ዓመታት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ልጃገረዶች ማረፊያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

ሴቶችን ብቻ ተቀብሎ የሚያስተናግደው ማዕከሉ በአዲስ አበባ ህጻናትና ሴቶች ቢሮ የሚተዳደር ሲሆን፥ በውስጡ ለሚገኙ ወላጅ አልባ ልጆች የምግብ፣ መጠለያና የአልባሳት ድጋፍ ይሰጣል።

You might also like
Comments
Loading...